ኮሚቴው በሀገር ውስጥ ህፃናት እንክብካቤ ላይ ለሚሰሩ ተቋማት ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ጠቆመ

(ዜና ፓርላማ)፣ መጋቢት 29/2013 ዓ.ም.፤ በኢ... ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ የሚገኘውን አብየኔዘር ሰፖርቲንግ ዴቨሎፐመንት አሶሴሽን ህጻናት ማሳደጊያ ጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱም ድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ አርጋው አየለ ድርጅቱ በ1998 ዓ.ም እንደተመሰረተና በወር ለኪራይ 80 ሽህ ብር በመክፈል ህጻናትን በማሳደግ ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት በጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ተጥለው የተገኙ እንደሆነና አንዳንዶቹ ደግሞ የአካል ጉዳተኛ መሆናቸውን አስረድተው ስራው ከተጀመረ 15 ዓመት ቢሆንም ቦታ እንዲሰጣቸው በየጊዜው ቢጠይቁም ትኩረት እንዳልተሰጣቸውና እስካሁን በችግር ላይ መሆናቸውን የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ላይ ከፍተኛ ስራ እንደሰራና ትምህርት ቤት ምግባም ላለፉት 5 ዓመታት በተከታታይ ለ51 ትምህርት ቤቶች 31‚700 ህጻናትን ምገባ ማድረጉንም አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለ3 ተከታታይ ዓመታት ተከራይተው እንደሚሰሩና ለልጆች አልጋ፣ ለትምህርት ቤት እና ለምግብ ከምናወጣው ወጭ በላይ ለቤት ኪራይ የምንከፍለው በጣም ወድ ነው ሲሉ አቶ አርጋው ለኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

ችግሩንም ለማቃለልም ሌሎች የለቀቁ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ይጠቀሙበት የነበረ ቦታ ስላለ እንዲሰጠን የከተማ አስተዳደሩን ብንጠይቅም እስካሁን ምላሽ ባለማግኘታችን ህጻናቱ በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ነው አክለው የተናገሩት፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ድርጅቱ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ህፃናት አገልግሎት የሚሰጥ ከመሆኑ አንጻር የተለያዩ ግብዓቶች ለአብነት የህጻናት አልባሳት፣ ልዩ ልዩ የአካል ድጋፎች ወደ ሀገር ውስጥ ከቀረጥ ነጻ የሚያስገባበት ሁኔታ እንዲፈጠር የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አመላክቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን አስተባባሪ የተከበሩ ወ/ሮ ሞሚና መሃመድ የቦታ ችግሩን ለማቃለል እንዲቻል የውጭ ድርጅቶች ጊዜአቸውን ጨርሰው በመውጣታቸው የተፈቀደው ቦታ ርክብክብ ቢደረግና የሴፊቲኔት ፕሮግራም ውስጥ መሳተፍ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር በሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ድርጅቱ በተለይ ለሀገር ውስጥ ህፃናት እንክብካቤ የሚያደርግና የሚደግፍ በመሆኑ ተቋሙ የሚከተለው የድጋፍ መርህ ህፃናት ጎዳና ሳይወጡ በደገፍና የችግሩን ምንጭ ማድረቅ ላይ ያተኮረ በመሆኑ በአግባቡ መደገፍ እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

ድርጅቱ ለከፍተኛ የስነ-ልቦና ጉዳትና ወጪ በመጋለጡ ቤት ተከራይቶ ከመስራቱ ባሻገር በጥበት ምክንያት ችግር እያጋጠመው ስለሆነ ከአሁን በፊት ፕሮጀክት ኮንቲኔት ይጠቀምበት የነበረውን ቤት ጊዜውን ጨርሶ ስለሄደ ለድርጀቱ እንዲሰጥ የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌደራል በጎ አድራጎት ኤጀንሲ በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለባቸው የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ ወ/ሮ ሞሚና አሳስበዋል፡፡ 

በመስፍን አለሰው