የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሴቶች ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች  አከበረ

መጋቢት 17/2013 ዓ/ም (ፓርላማ)፡- በአለም አቀፍ ለ11ዐኛ በሃገራችን ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሴቶች ቀንን የምክር ቤቱ አባላትና የጽ/ቤቱ ሠራተኞች  በደማቅ ሥነ ሥርዓት አከብረውታል፡፡

በዓሉ  “የሴቶችን ሁለተናዊ መብት የሚያስከብር ማህበረሰብ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው፡፡

በዚሁ ጊዜ  በም/ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የሴቶች ኮከስ ሥራ አስፈፃሚ የተከበሩ ወ/ሮ አበባ ዬሴፍ ሴቶችን  በሁሉም ዘርፍ ተሳትፎአቸውንና ተጠቃሚነታቸውን  በላቀ ደረጃ  ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ የሴቶች ከወንዶች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን  ወ/ሮ አበባ አስታውሰው፣   ለአብነትም የሃገሪቱን ኘሬዘዳንት ጨምሮ   በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚኒስትርነት ከተሾሙት ግማሽ ያህሉ ሴቶች መሆናቸው የሴቶችን በውሳኔ ሰጪነት ያላቸውን ተሳትፎ ያሳየ እንደሆነ ግልፀው ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

በበአሉ ላይ በሴቶች መብትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የተዘጋጀ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የሻማ ማብራትና የዳቦ ቆረሳ ሥነ ሥርዓትም ተከናውኗል፡፡

በአሉ ከማርች 8 ጀምሮ ለአንድ ወር  “የሴቶችን ሁለተናዊ መብት የሚያስከብር ማህበረሰብ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል በሃገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡