የማምረቻ ፋብሪካውን ትርፋማነት ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

(ዜና ፓርላማ) ፣ መጋቢት 29 ፣ 2013 ዓ.ም.፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ አስፈላጊውን ጥገና በማድረግ ትርፋማነቱን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህንን የገለጸው የፋብሪካውን የስራ አፈጻጸም እና ያጋጠሙትን ችግሮች አስመልክቶ ሰሞኑን በቦታው ተገኝቶ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

ፋብሪካው ባጋጠመው የእርጅና እና የጥገና ችግሮች ምክንያት የእቅድ ክንውኑ ዝቅተኛ መሆኑን የመስክ ምልከታ ቡድን አስተባባሪው የተከበሩ አቶ አያሌው አይዛ አንስተው፤ መለዋወጫ እቃዎች በወቅቱ በማቅረብ እና የጥገና ስራ በመስራት የፋብሪካውን ትርፋማነት ማሳደግ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

የስራ እድል ፈጠራ አቅዶ አለመስራት፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች  እና  የለውጥ መሳሪያዎች አተገባበር  እንዲሁም  የሽያጭና ገበያ አለማፈላለግን  ቡድኑ በእጥረት ጠቅሷል፡፡

ከፋብሪካው የሚወገዱ ኬሚካሎች በአግባቡ ታክመው የሚወጡ መሆናቸውን እና ፋብሪካውን መልሶ ለማደራጀት ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት መጀመሩን ቡድኑ በጥንካሬ አንስቷል ፡፡

የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ ቃበቶ በበኩላቸው የፋብሪካውን ትርፋማነት ለማሳደግ በቅርቡ የጥገና ስራ እንደሚጀመር አስረድተዋል፡፡  

ፋብሪካው ከተቋቋመ 28 አመት የሆነው በመሆኑ እና የሚያመርታቸው ምርቶች የአሲድ ውሕዶች በመሆናቸው የማምረቻ መለዋወጫዎቹ በቀላሉ እንደሚጎዱ ስራ አስኪያጁ ገልጸው፤ ይህም በትርፋማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አብራርተዋል፡፡  

ፋብሪካው የገጠመውን ችግር ለሚመለከተው አካል ማስረዳታቸውን እና የጥገና ስራውን ለማስጀመር 170 ሚሊዮን ብር መፈቀዱን አቶ አድማሱ ተናግረው፣ በጥገና ስራው ለሚሳተፉ ድርጅቶች ጨረታ የማውጣት ሂደት ላይ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በፋንታዬ ጌታቸው