የተጎዱ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ የኮሚሽኑ ሚና የጎላ እንደነበር ቋሚ ኮሚቴው ገለጸ፤

(ዜና ፓርላማ)፣ መጋቢት 28/2013 ዓ.ም፤ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በሀገረችን በሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ የሚጎዱ ዜጎችን በመደገፍ እና መልሶ በመቋቋም ረገድ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ገልጿል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን የገለጸው ሰሞኑን በአዲስ አበባና አከባቢው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ በተመለከተበት ወቅት ነው፡፡

በሀገራችን በተከታታይ እየተፈጠረ ያለውን የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ለመቋቋም ይቻል ዘንድ፤ በተለይም በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የኮሚሽኑ አመራሮችና በየደረጃው ያሉ ሰራተኞች በመቀናጀት ሕዝብ እና መንግስት የጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ያደረጉት ጥረት የሚያስመሰግን መሆኑን የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል እና የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ ወ/ሮ ብርቱኳን ሰብስቤ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በየቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በግጭት እንዲሁም በጎርፍ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከማድረሱም በላይ፤  ለምግብ እርዳታ፣ ለገበያ ማረጋጋት፣ ለልማታዊ ሴፍቲኔት እና ለመደበኛ ተረጂዎች ያዳረሰ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ማረጋገጥ ችሏል፡፡

ይሁንና የዋና መ/ቤት ቢሮ ዲዛይንን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በወቅቱ በማጠናቀቅ የክምችት አቅምን አለማሳደግ፣ የካፒታል በጀት አፈጻጻም ዝቅተኛ መሆን፣ የስራ አካባቢ ለሰራተኛው ምቹ ያለመሆን፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እና የደሞዝ ክፍያ ለሰራተኞቹ በጊዜው ያለመድረስ ችግር እንዲሁም ሰራተኞችን ከማብቃት አኳያ በስልጠና ያለማገዝ ችግሮች በፍጥነት መቀረፍ እንዳለባቸው የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠቁመዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አያይዞም ኮሚሽኑ ለተለያዩ ተቋማት የሚሰጠው የምግብ እህል እና  ቁሳቁሶች ብድር ሳይመለስ አሁንም እያበደረ መሆኑ ለተለያዩ ችግሮች የሚያጋልጥና በቀጣይ የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን  ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሣ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የአስር ዓመት ዕቅድ የተጠናቀቀ መሆኑና በዕቅዱ ከተካታቱት የሪፎርም ስራዎች መካከል፡- ዘመኑን የዋጀ የሰው ኃይል ግንባታ፣ ዘመኑ ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ግብኣቶች የታገዘ ተቋማዊ አገልግሎት ማቋቋም፣ የምግብና ምግብ ነክ አቅርቦትን ክልሎች እንዲሰሩ እንዲሁም በሴክተር መስሪያ ቤቶች እና በሚመለከታቸው ሁሉ የማካተት እና የማስረፅ ስራዎች ዋና ዋናዎቹ ስለመሆናቸው ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አያይዘውም በቋሚ ኮሚቴው እንደ ውስንነት የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት እና ለመቀነስ ከሰራተኛው እና በየደረጀው ከሚገኙ አመራር አካላት ጋር በመተበባር እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

በ ሚፍታህ ኪያር