የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ የዜጎችን መብትና ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ተሻሽሎ መቅረቡን ኮሚቴው አስታወቀ፡፡

(ዜና ፓርላማ) መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም፤ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴርና ከባለ ድርሻ አካት ጋር በውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ማሻሻያ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ በ2011 ዓ.ም ፀድቆ ሰራ ላይ ቢውልም ወደ ተግባር ሲገባ አላሰራ ያሉ፣ ያጋጠሙ እንቅፋቶችና ውስንነቶች በመኖራቸው የአዋጁ መሰረት ሳይነካ የተለያዩ ማሻሻያዎችን አካቶ ሊቀርብ ችሏል ብለዋል፡፡

በአዋጁ ላይም ወደ 22 የሚጠጉ አንቀጾች እንዲሻሻሉ መደረጉን ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል፡፡ በተለይ አዋጁን ቀደም ሲል የውጭ አገር የስራ ስምሪት መንግስት ለመንግስት በሚደረግ ግንኙነት ብቻ እንደነበርና ይህም አላሰራ ያለ መሆኑን ወ/ሮ አበባ አውስተው አሁን ግን በ3 የስምሪት አይነት ማለትም መንግስት ለመንግስት፣ ኤጀንሲ ለኤጀንሲና ኤጀንሲው የሚልካቸው ሰራተኞች እንደሚኖሩም ነው ያስረዱት፡፡

አክለውም ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ የቤት ሰራተኛ ብቻ የሚያካትት ብቻ እንደነበረ አሁን ግን ሙያ ያላቸውና የተማረ የሰው ሃይል መንግስት ለመንግስት በሚኖር ግንኙነት  የሚላክበት ሁኔታ በማሻሻያው መካተቱን ነው ያብራሩት፡፡

በተጨማሪም ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ላይ ኢትዮጵያዊያን ብቻ በስራው እንዲሳተፉ ይገድብ እንደነበር አሁን በቀረበው ማሻሻያ ላይ ግን ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ አገር ዜጎች በዘርፉ ላይ በህጉ በተገደበ መንገድ በስምሪቱ ላይ እንዲሳተፉ የሚያግዝ ነውም ብለዋል፡፡

የትምህርት ዝግጅትንም በተመለከተ ቀደም ሲል 8ኛ ክፍል ያጠናቀቀ ብቻ በውጭ አገር ይሰመራ እንደነበረ አሁን ግን ሙያውና ክህሎቱ ያለው ማንኛውንም ግለሰብ በስራው ላይ እንዲሳተፍ በረቂቅ አዋጁ ላይ መካተቱንም ነው የተናገሩት፡፡

የተሻሻለው አዋጅ በውስጡ የዜጎቻችን ደህንት፣ ክብርና ውጭ አገር ከሄዱ በኋላ መብታቸው ተከብሮና የተሻለ ገንዘብ አግኝተው ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውንም ሊጠቅሙ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያመቻች እንደሆነም ነው አክለው የገለጹት፡፡

በመጨረሻም ከኤጀንሲዎች በተለይ ደግሞ ከቴክኒክና ሙያ የትምህርትን ዋጋ የሚያሳጣ ስለሆነ የትምህርት ጉዳይ ይታይ የሚል አስተያየት መቅረቡን አመልክተው በቀጣይ ቋሚ ኮሚቴው ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በሚኖረው መድረክ ተወያይቶና የውሳኔ ሀሳብ አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ እንደሚያቀርብም ሰብሳቢዋ አስረድተዋል፡፡

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው የተሻሻለው የውጭ አገር የስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ መንግስት የዜጎችን መብትና ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ በአግባቡ መታየቱን አስረድተዋል፡፡  

የውጭ አገር የስራ ስምሪት በአግባቡ መመራት ስላለበት ኤንሲዎች ስራ አስኪያጅ ሲቀጥሩ ዲግሪ ያላቸው እና የሚመለከታቸውን የትምህርት ዝግጅት ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በመስፍን አለሰው