“የጥብቅና አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግ እየተሰራ ነው”  የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

(ዜና ፓርላማ)፣ ሚያዝያ 04፣ 2013 ዓ.ም.፤ የጥብቅና አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ ተናገሩ፡፡

ምክትል ዐቃቤ ሕጉ ይህንን የገለጹት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል የጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡

 በውይይቱም ተጠሪ ተቋማትን ጨምሮ የሕግ ባለሙያተኞችና ምሁራን የተገኙ ሲሆን ፣ጠበቆች በአገራችን የተሻለ አገልግሎት በመስጠት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማስቻል እንዲሁም የህዝብ ጥቅምን በማስጠበቅና ፍትሕን በማስፈን ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ነው አቶ ተስፋዬ የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት ያብራሩት፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በጥብቅናው ዘርፍ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በይዘቱ በርካታ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉት ጠቅሰው፣ የሕዝቡን የፍትሕ ፍላጎት ለማስጠበቅ  ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሴ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ  ሕብረተሰቡ ጥራት ያለው እና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ በር የሚከፍት መሆኑን ገልጸው፣  በረቂቁ ላይ «ልዩ የጥብቅና ፈቃድን» በተመለከተ የተቀመጠው ሃሳብ በምን ሁኔታ እንደሚሰጥ አዋጁ የሚያስቀምጥ ባለመሆኑ በትኩረት ሊታይ ይገባል ብለዋል፡፡

በኢያሱ ማቴዎስ