News News

የምክር ቤቱ ሥራዎችን ለማሻሻል ለቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ሥልጠና ተሰጠ፡፡

ምክር ቤቱ የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት እንዲችል የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች አቅም ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ተገለፀ፡፡

ይህ የተጠቆመው በብሾፍቱ ከተማ ለተከታታይ 4 ቀናት በቀጣይ የምክር ቤቱን ስራዎች የበለጠ ለማሳለጥ እና ዘርፈ-ብዙ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ለቋሚ ኮሚቴ አመራሮች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በሙሁራን በተሰጠው ስልጠና ላይ ነው፡፡

የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስ የሆኑት ዶክተር ምህረት ደበበ ‹‹ህሊና›› በተሰኘ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ በመስጠት የምክር ቤቱ አባላትና አመራሮች ለወከላቸው ህዝብ ስራዎችን በነፃ ህሊና ማከናወን እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

የአገሪቱ ህገ-መንግስት የህዝቦችን የሞራል ህሊና ያካተተ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ምህረት ደበበ የህሊናን ጠቀሜታና አስፈላጊነት በኮምፓስ፣ በወንፊት፣ በመስታዎት እና በሞተር ምሳሌነት ገልጸውታል፡፡

ዶ/ር ፕሮፌሰር ኤሊያስ ኑር በበኩላቸው ምክር በቱ በስራው ስኬታማ እንዲሆን በህግ መንግስቱ የተሰጠውን ስልጣን በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ እና በሚቀርቡለት ውሳኔዎች ላይ በሳል ውይይቶችና ክርክሮች ማድረግ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

የምክር ቤቱን ስራ ከአገሪቱ ህገ መንግስት ጋር በማያያዝ ሰፊ ገለጻ ያደረጉት ዶክተር ኤሊያስ በህዝቡ ዘንድ የመሰረተ ልማቶች አገልግሎት አሰጣጥ፣ በተፈትሮ ሀብቶች እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ላይ የተጋረጠባቸውን የመጥፋት አደጋ፣ አንዲሁም የመሬትና የማንነት ችግሮች የሚያስከትሉትን ቀውስ በየደረጃው ለመፍታት በትኩረት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይም የንግድ፣ የኢንሹራንስና ሌሎች በየጊዜው ማሻሻያ የሚደረግባቸው ህጎች ለህዝቡ ተደራሽነት የላቸውምና በድህረገጽ መለቀቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የUNOPS ኦፕሬሽናል ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ወርቅነሽ መኮንን የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በእውቀትና ክህሎት ላይ ተመስርተው ፕሮጀክቶችን መከታተል እንዲችሉ የክትትል ስልቱን ማዘመን እንደሚያስፈሰልግ ገልጸው በጀትን ጨምሮ የፕሮጀክቶችን ጥራት፣ ሂደት አፈጻጸምና የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በዝርዝር የሚያሳዩ ማንዋሎች መኖራቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

በፕሮጀከቶች ላይ የሚደረገው ክትትል በቂ ባለመሆኑ አገሪቷ የግምገማ ፖሊሲ ህግ ቢኖራት የተሻለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ረዳት ዳይሬክተር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ በሰጡት የኮሚዩኒኬሽን ስልጠና በአገራችን የሚስተዋሉ ችግሮችን በበሰለ ውይይት ለመፍታት የተግባቦት ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በአንፃሩ፣ ለግጭቶች መከሰት መንስኤ ባመዛኙ ከተግባቦት ማነስ የመነጨ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤቱ ስራዎች ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የተግባቦት ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

የUSNRC ሲኒየር ማናጀር ዶክተር ደረጀ ተሰማ አመራርነትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ምክር ቤቱ የሚቀርቡለትን ውሳኔዎች እጅ አውጥቶ ከማፅደቅ ባለፈ በሳል ውይይቶችና ክርክሮች በማድረግ ለህዝብ የሚጠቅሙ አሰራሮች እንዲተገበሩ መታገል እንዳለበት እና የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል በሚደረገው ሁለንተናዊ ርብርብ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ምስራቅ መኮንን በስልጠናው ዙሪያ በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቶች ተጀምረው አስከሚጠናቀቁ ድረስ በዘርፉ ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ተደርጎ ተጨባጭ መረጃዎች ተይዘው በምክር ቤቱ አባላት ጥልቅ ውይይት እንዲደረግበት እና ምክር ቤቱ ከህዝቡ ጋር የሚገናኝበትን የተግባቦት ስልት እንዴት መዘርጋት እንደሚቻል ግብአቶች የተግኙበት ነው ብለዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ስልጠናው በሁሉም መስክ ውጤታማ ፓርላማ መፍጠር የሚያስችል እንደሆነ ገልጸው ተባብረን ከሰራን ለውጥ የማናመጣበት ምክንያት አይኖርም እድሉ በእጃችን ነው ብለዋል፡፡