News News

ምክር ቤቱ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቷል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡

ምክር ቤቱ ህዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል መንግስት አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ቁጥር1097/2011 ለማሻሻልና ለማጠቃለል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የመንግስት ተጠሪ ረዳት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጫላ ለሚ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በአዋጁ ላይ የተለያዩ ተቋማት ድልድልን በሚመለከት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ መሆን የሚገባቸው ለአንድ ሚኒስቴር የተሰጠበት ሁኔታ መኖሩንና ሌሎች ጉዳዮች በዝርዝር ታይተውና ተስተካለው መጽደቅ እንዳለበት በማንሳታቸው ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 4/2011 ሆኖ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡

በመቀጠል የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን የኮሚሽኑ ዋና አላማ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍትህ፣ ብሔራዊ አንድነትና መግባባት እንዲሁም እርቅ እንዲሰፍን መስራት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱም በስፋት ተወያይቶበት ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 5/2011 ሆኖ በዋናነት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በተባባሪነት ለህግ፣ ፍትህና ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

በማስከተልም የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለማቋቋም በቀረበ ረቂቅ አዋጅን ላይ የመንግስት ተጠሪ ረዳት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጫላ ለሚ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከማንነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችን የፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲመለከት በህገ-መንግስቱ ስልጣን ተሰጥቶት ሳለ አዲስ ኮሚሽን ማቋቋም ለምን አስፈለገ? የሚለው በም/ቤቱ አባላት ከተነሱት ጥቄዎች መካከል ይገኝበታል፡፡ 

ከም/ቤት አባላት የተነሱትን ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ታሳቢ በማድረግ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 6/2011 ሆኖ በዋናነት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በተባባሪነት ለህግ፣ ፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ4 ተቃውሞና በ1 ድምጸ ተአቅቦ  በአብላጫ ድምጽ ተመርቷል፡፡

በመጨረሻም ም/ቤቱ የምክር ቤቱን 4ኛ አመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡