News News

አገሪቱ ላይ ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ ሳቢያ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት አዳዲስ የውጪ ባለሃብቶችን ለመሳብ ተቸግሮ መቆየቱን የኢነቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡

አገሪቱ  ላይ  ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ ሳቢያ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት አዳዲስ የውጪ ባለሃብቶችን ለመሳብ ተቸግሮ መቆየቱን የኢነቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ አገሪቱ ላይ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት አዳዲስ ባለሃብቶችን መሳብ አለመቻሉንና ነባር ባለሀብቶችን አረጋግቶ በማቆየት ስራ ላይ ተጠምዶ መቆየቱን የ2011 በጀት አመት የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቱን ለንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት አስረድቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሸን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ እንደገለጹት ኮሚሽኑ 230 ለሚጠጉ የውጭ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዙሪያ ገለጻ የተደረገላቸው መሆኑንና በበጀት አመቱ ከታቀዱት 49 ፕሮጀክቶች ውስጥ 25ቱን በመለየት ለህብረተሰቡ ከሚሰጡት ጥቅም አኳያ ጥናት አካሂደናል በማለት  ለቋሚ ኮሚቴው አብራርዋል፡፡

የ3 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማለትም ሀዋሳ፣ መቀሌና ኮመቦልቻ የመጀመሪያና የመጨረሻ ርክክብ ሂደት ላይ እንደሚገኙና የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ዋና ግንባታዎች የተጠናቀቁ በመሆኑ መመረቃቸውንና ፓርኮቹ እየገቡ ላሉት ባለሀብቶች ዝግጁ መሆናቸውን ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል፡፡

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያጋጠመውን የውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ስራ ተቋራጩ ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ክልል ውጭ የውሃ አቅርቦት አማራጭ ቦታ በማጥናት እንዳቀረበና በተመረጠው ቦታ ላይ 600 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ተቆፍሮ መጠናቀቁንም አቶ ፍጹም ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች በእቅድ የተያዙ ስራዎችን ለማከናወን የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ማነቆ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኤሌክትክ አገልግሎት ያሉበት የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝም ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

ዘላቂ የኤሌክትክ ሀይል አቅርቦትን በተመለከተ የአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን የማገናኘት ስራ እንዲሁም ቦሌ ለሚና ቅሊንጦ የተጀመሩትን ሳብስቴንሽ ግንባታዎችና ትርንስሚሽን ዝርጋታዎችን የማፋጠን ስራ የሚጠይቅ እንደሆነና በቀሪዎቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይ በአዳማና ድሬዳዋ  ባለሀብቶች በመግባት ላይ የሚገኙ ቢሆንም ከዘላቂ ኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ረገድ የተጀመረ ስራ ስለሌለ በመንግስት በኩል ልዩ ድጋፍና ትኩረት የሚጠይቅ እንደሆነም አቶ ፍጹም ተናግረዋል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተካ ሀይለየሱስ በበኩላቸው የእቅድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንደሆነና በተለይ ከስራ እድል ፈጠራና ኢንቨስትመንት ፍሰት አኳያ በእቅዱ መሰረት እንዳልተሰራ ገልጸው በአገሪቱ ውስጥ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት አዳዲስ ኢንቨስተሮችን መሳብ ሳያሆን ያሉትን መደገፍና ማቆየት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሰሩ እንደነበር አስረድተው በሩብ ዓመቱ 56 በመቶ ብቻ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ስራዎችን የተደራጀ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ተጠቅሞ ለመስራት አይ-ጋይድ የኢንቨስትመንት ጋይድ ማንም ኢንቨስተር የፈለገውን በማህበራዊ ሚዲያ የማግኘትና ንግድና ኢንዱስትሪ ምን እንደሚመስል የማወቅ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ አገልግሎቶችን በኢንተርኔት የማግኘት መብታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረው በቀጣይም ጅማና ድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመርቀው ወደስራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጌታቸው  መለሰ እንዳሉት ኮሚሽኑ 54 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመመዝገብ አቅዶ 42ቱ ማከናወኑ፣ መረጃዎችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ተደራሽ ማደረጉና በኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉ  በጠንካራ ጎን የሚታይ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የዜጎች የስራ እድል ፈጠራ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑ በተለይም 41ሽ ታቅዶ 5ሽ ብቻ መከናወኑ፣ ቋሚ ኮሚቴው ለተቋሙ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ምንጮችን ለይቶ የማክሰሚያ ስልቶችን እንዲያስቀምጥ በተደጋጋሚ ግብረ-መልስ ቢስጥም አሁንም አለማሻሻሉና ኢንዱስትሪዎችም ጀኔሬተር እንዲያዘጋጁ ጥረት አለመደረጉ በደካማ ጎን አንስተው በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ሲሉ አቶ ጌታቸው አሳስበዋል፡፡