Participate

የፌዴራል የአስተዳደር ስነ-ስርአተ ረቂቅ አዋጅ

 
የፌዴራል የአስተዳደር ስነ-ስርአተ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተዘጋጀ አጭር ማብራሪያ
 
 መግቢያ
 
ህጉን ለማርቀቅ የተቋቋመው ኮሚቴ ህጉን ከማርቀቁ በፊት የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ሊገዛቸው የሚገቡ ጉዳዮች  የትኞቹ መሆን እንዳለባቸው የለየ ሲሆን፤ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ መግቢያ፤ ትርጓሜንና ልዩ ልዩ የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎችን ጨምሮ፡-
 • የአስተዳደር ተቋማት በህግ በሚሰጣቸው የውክልና ሥልጣን የህግ አውጪነት ተግባር የሚያከናውኑ ስለሆነ ህጉን የሚያወጡበትን ሥነሥርዓትና መርሆዎች፤
 • የአስተዳደር ተቋማት አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የሚሰጡበትን ሥነሥርዓት ሂደትና ሊከተሉ የሚገባቸውን መርሆዎች፤
 • የአስተዳደር መመሪያዎችና አስተዳደራዊ ጉዳዮች  ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ የሚከለሱበትን ሥነሥርዓት የሚደነግጉ ክፍሎች ሊኖሩት እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደራዊ የዳኝነት አካላት (Administrative Tribunals) የሚመሩበትን የሥነሥርዓት ደንብ የዚሁ አዋጅ አካል መሆን ይኖርበት እንደሆነ የሃሳብ ልውውጥ የተደረገ ቢሆንም፤ አስተዳደራዊ የዳኝነት አካላት እጅግ በጣም በልዩ ሁኔታና በውስን የአስተዳደር ተቋማት ሥር የሚዋቀሩ በመሆናቸው፤ ምን ዓይነት ጉዳዮች እንደሚያስተናግድና ምን ዓይነት የሥነ ሥርዓት ሂደት እንደሚከተል ከማቋቋሚያ አዋጃቸው መረዳት ስለሚቻል ፤ አስተዳደራዊ የዳኝነት አካላትን የሥነሥርዓት ደንብ በዚህ አዋጅ ማካተት እንደማይገባ ተወስኖ ሦስቱ ዋነኛ ጉዳዮች ላይ ብቻ በማትኮር ረቂቁ ሊዘጋጅ ችሏል፡፡
ይህ የማብራሪያ ሰነድ ረቂቅ አዋጁን ድንጋጌዎች በአንቀጽና በንኡስ አንቀጽ ደረጃ ለማብራራት ያለመ ሳይሆን የረቂቁ አንኳር ናቸው ተብለው በታመኑ ነጥቦች በማብራራት ጉዳዮች የተወሰነ ነው፡፡ ዓላማው ረቂቁ ይዟቸው የመጡት አዳዲስ ሃሳቦችና አሠራሮች ለፈጻሚዎችም ሆነ ለተገልጋዮች ጠቅለል ባለ መንገድ ለማብራራት ነው፡፡
 
           
የአዋጁ ቅርፅ እና ይዘት
1. ክፍል አንድ (አንቀጽ 1፣2 እና 3)
የአዋጁ መግቢያ የአስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ ሊያሳካቸው የሚገቡ ሕገመንግስታዊ ዓላማዎች በመግለፅ የዜጎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስተዳደር ተቋማት ያለአግባብ እንዳይሽራረፉ የአስተዳደር ተቋማት የውክልና ሥልጣን በሕግ እና በሥነሥርዓት ማዕቀፍ መመራት እንደሚያስፈልገው፤ እንዲሁም ይህ ሥልጣንና ተግባር በፍርድ ቤት የክለሳ ሥነ ሥርዓት ቁጥጥር ሊደረግበት የሚቻል ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡
እስከአሁን ባለን አሠራር የአስተዳደር ተቋሞች ስለ ህግ  አወጣጣቸውና ውሳኔ አሰጣጣቸው አስመልክቶ እንዲሁም በእነዚህ ተግባሮቻቸው ቅር የተሰኙ ወገኖች ስለሚኖራቸው መፍትሄ የተቀመጠ ሥርዓት ባለመኖሩ የዘፈቀደ አሠራር ስፍኖ ክፍተኛ የመልካም አስተዳደር እጦት ምንጭ ከሆኑት ጉዳዮች  አንዱ ሆኖ መቆየቱ በተለያዩ መድረኮች የተገለፀ ሲሆን  መንግስትም አምኖ የተቀበለው ድክመት ነው፡፡ ይህ አዋጅ በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት በመድፈን የድርሻውን ይወጣል ተብሎ ይታመናል፡፡
የአዋጁ  ክፍል  አንድ የአዋጁ ስያሜ፤ የቃላትና ሀረጎች ትርጓሜ፤ የአዋጁን የተፈፃሚነት ወሰን የሚገዙ ድንጋጌዎች የያዘ ሲሆን በሌላ  ክፍል  ካሉ አንቀጾች ጋር በመናበብ መሰረታዊ መርሆችን የሚደነግጉ ትርጉሞችም ተካተውበታል፡፡
ለምሳሌ “የአስተዳደር ተቋም” የሚለው ቃል በፌዴራል መንግስት አስፈጻሚ አካል ሥር የተደራጁ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እና ለፌደራል  መንግሥት ተጠሪ የሆኑትን የከተማ አስተዳደሮችን አስፈፃሚ አካላትን አካቶ የተተረጎመ ነው፡፡ በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ የክልል የአስተዳደር ተቋሞችን የሚሸፍን አይደለም፡፡ እዚህ ላይ  ከዜጎች ጋር በእለት ተእለት የሥራ ግንኙነት ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው የክልል የአስተዳደር እርከኖች ሆነው እያለ እነርሱን የማይሸፍን አዋጅ ውጤታማነቱ ምን ያህል ነው ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ለምንስ እንዲህ ዓይነት ውሱን ተፈጻሚነት  አዋጅ እንዲወጣ ተወሰነ የሚል ተገቢ ጥያቄም ሊቀርብ ይችላለ፡፡
ነገር ግን ይህ ነጥብ ከፌደራልና ክልል የሥልጣን ክፍፍል አንጻር መታየት ያለበት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በፌደራል የመንግስት አደረጃጀት መንግስታዊ ሥልጣን በሁለት ደረጃ የሚከናወን ነው፡፡ እነዚህም በፌደራል ደረጃና በክልል መስተዳደሮች ደረጃ ናቸው፡፡ ከመንግስታዊ ሥልጣኖች አንዱ የህግ ማውጣት ሥራ ነው፡፡ በመሆኑም ህግም በፌደራልና በክልል  ደረጃ የሚወጣ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ፌደራል መንግስቱም ሆነ ክልሎች የየራሳቸው የአስተዳደር ተቋሞች ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ በህገ መንግስቱ የሥልጣን ክፍፍል መሠረት የፌደራሉ ህግ አውጪ አካል ለፌደራል  የአስተዳደር ተቋሞች የሚያገለግል፤ የክልል ህግ አውጪ አካላት ለየክልላቸው አስተዳደር ተቋሞች የሚያገለግል ህግ ያወጣል ማለት ነው፡፡ ይህ አዋጅ ደግሞ በፌደራል ህግ አውጪ አካል እንዲታወጅ የተዘጋጀ ስለሆነ ተፈፃሚነቱ በፌዳራሉ የአስተዳደር ተቋሞችና ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለፌደራል መንግስቱ ለሆነ የከተማ አስተዳደሮች ነው፡፡ ክልሎች ይህንን አዋጅ እንደ መነሻ ሰነድ ተጠቅመው የራሳቸውን አዋጅ የማውጣት እድል ግን ክፍት ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ ረቂቅ የተፈጻሚነት ወሰን በፌደራል አስተዳደር ተቋሞችና በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተወሰነ ነው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፣ የዐቃቤ ህግ የፖሊስ፣ የመከላከያና የደህንነት ተቋሞችም ከአገልግሎት አሰጣጥና መመሪያ አወጣጥ ተግባራት ውጪ ያለው ስልጣናቸው ከአዋጁ የሥልጣን ወሰን ውጪ ተደረገዋል፡፡ እነኚህ ተቋሞች ከአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን ውጪ የተደረጉበት ምክንያቶች አለ፡፡ የአስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ ዋነኛ ከሚባለት ዓላማዎች አንደ መንግስት ከመደበኛው የህግ-አስከባሪነት ሥልጣኑ በተጨማሪ ገበያ እና ማህበራዊ ሕይወትን የመቆጣጠር ሥልጣኖችንም እያካተተ በመምጣቱ፤ ለዚህ የመቆጣጠር ሥልጣን ገደብ ማበጀት ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ዐቃቤ ህግ፣ ደህንነት፣ ፖሊስ እና መከላከያ ያለ ነባር የሕግ አስከባሪ ተቋማት የተቋቋሙበትን ዋና ስራ በተመለከተ እንደ አስተዳደር ተቋማት ተቆጥረው የአስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ የሥልጣን ወሰን ሥር አይወድቁም፡፡ ሆኖም መመሪያ ሲያወጡ እና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ሲሰጡ በዚህ መመሪያ የሚገዙ ይሆናል፡፡
በመጨረሻም ብሄራዊ ባንክ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የሚያወጣቸው መመሪያዎች ከፍተኛ ሚስጥር ያለባቸው በሆኑ ጊዜ የአዋጁን የተወሰኑ ድንጋጌዎች እንዳይከተል ለማድረግ ተሞክሯል፡፡
ሌላው በዚህ  ክፍል  መወሳት ያለበት ነጥብ በአዋጁ ሥር ትርጓሜ የተሰጣቸው ጥቂት ቃላትና ሀረጎች አሉ፡፡ ይህም መመሪያ ሲሆን በረቂቅ አዋጁ “መመሪያ” ማለት ህግ አውጪው አካል በሚሰጠው የውክልና ሥልጣን መሠረት በአስተዳደር ተቋም የሚወጣና በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ጉዳዮች  ውጤት የሚያስከትል ሰነድ ነው ይለዋል፡፡ ደንብ በዚህ አዋጅ ውስጥ እንዲካተት አልተደረገም፡፡ ይህ እርምጃ የአዋጁን ሁለት ዋነኛ አቋሞች ይጠቁማል፡፡ የመጀመሪያው የአስተዳደር ሥነሥርዓት ረቂቅ ሕጉ ሊቆጣጠረው የሚፈልገው የህግ ሰነድ “መመሪያ” ብቻ መሆኑን እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጣውን “ደንብ” የተባለ ከመመሪያ ከፍ ከአዋጅ ደግሞ ዝቅ ያለ የሕግ ሰነድ ከዚህ አዋጅ የተፈጻሚነት ወሰን ውጪ መደረጉ ነው፡፡
ይህም የሆነበት ምክንያት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስፈፃሚው ክፍተኛው የሥልጣን አካል እና ፖሊሲ አመንጪ ሆኖ ከመስራቱ ባሻገር ዜጎችን በየእለቱ የሚያስተናግድ የአስተዳደር አገልግሎት ሰጪ ተቋም አለመሆኑ እና በአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጅ ስር ያለ ዝርዝር የሥነሥርዓት ሂደቶች ለመደበኛ የአስተዳደር ተቋም እንጂ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አሠራር የማይሆኑ በመሆናቸው ነው፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውክልና እንጂ የራሱ የሆነ ህግ (ደንብ) የማውጣት  ስልጣን የልለው በመሆኑ፤ ምክር ቤቱ ”ደንብ” ሲያወጣ ሊከተላቸው የሚገቡ ሥነሥርዓቶች እና መርሆች እንዲሁም እነኚሁ በተጣሱ ጊዜ ዜጎች ጥሰቱን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው የሚያስከልሱበት ሂደት የህግ ዝግጅትና ሕግ አወጣጥ ሥነሥርዓትን የሚደነግግ አዋጅ እንደሚኖር ታሳቢ የተደረገ በመሆኑ የደንብ ጉዳይ በዚያው ቢስተናገድ ይሻላል የሚል አቋም ተወስዷል፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ ለመመሪያ የተሰጠው ትርጓሜ ውስጥ ”መመሪያ” በሰዎች ማለትም በተገልጋዮች መብት ወይም ጥቅም ጉዳዮች  ውጤት ያለው የሕግ ሰነድ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይህ በራሱ ሁለት እንደምታ የሚኖረው ሲሆን በአንድ በኩል በዜጎች መብት እና ጥቅም ጉዳዮች  ውጤት የሌላቸው የአስተዳደር ተቋማትን ማለትም የአስተዳደር ተቋሙ ውስጣዊ አሰራር ብቻ የሚደነግጉ “መመሪያዎች” ከዚህ አዋጅ የሥልጣን ወሰን ውጪ መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማንኛውም በአስተዳደር ተቋማት የሚወጣ፤ በዜጎች መብት እና ጥቅም ጉዳዮች  ውጤት ያለው ሰነድ መመሪያ ተብሎ እንደሚጠራ እና መውጣት የሚገባውም በአዋጁ የተደነገጉ ሥነ ሥርዓቶችን በመከተል ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ይህም አሁን ባለው የአስተዳደር ተቋማት ወጥነት የሌለው ተለምዶአዊ አሰራር እንደ ማኑዋል፣ ጋይድላይኖች፤ ሰርኩላር እና የመሳሰሉት ሰነድች በሰዎች መብት እና ጥቅም ጉዳዮች  ውጤት እስካላቸው ድረስ መመሪያ ተብለው እንዲወሰዱ እና የመመሪያ አወጣጥ ሥነሥርዓትን ተከትለው እስካልወጡ ድረስ ሕጋዊ ውጤት እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይህም ያለው ተለምዶአዊ አሠራር የህግነት ውጤት በሌላቸው መሰል ሰነዶች መብት እና ግዴታዎች የሚጣለበትን ያልተገባ አሰራር ያስቀራል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
 
 • ክፍል ሁት (አንቀጽ 4-19)
 
የረቂቅ አዋጁ  ክፍል  ሁለት ስለ አስተዳደር መመሪያዎች አዘገጃጀት፤ማጽደቅና ምዝገባ አስመልክቶ የተለያዩ ድንገጌዎችን የያዘ ሲሆን በውስጡ ሦስት ንኡሳን ክፍሎችን አካቷል፡፡ ንዑስ  ክፍል  አንድ ስለመመሪያ አወጣጥ  የሚደነግግ ነው፡፡ የአስተዳደር ተቋማት በህግ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት መመሪያ እንደሚያወጡ  የተደነገገ ሲሆን፣ የአስተዳደር ተቋም መመሪያ የሚያወጣው በዚህ አዋጅ በተደነገገው ሥነ-ሥርዓት መሠረት ብቻ መሆኑን  ተመልክቷል፡፡
 
በአንቀፅ 5 ላይ ማንኛዉም የአስተዳደር ተቋም ሊያወጣ የሚገባውን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ማዉጣት አለበት የተደነገገ ሲሆን ”በተገቢው ጊዜ” የሚለው አገላለጽ ለትርጉም ክፍት እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም ክፍት የተተወበት ምክንያት ግን ሁለት ነው፡፡ አንደኛው አዋጅ መመሪያ የማውጣትን የውክልና ሥልጣን ለአስተዳደር ተቋማት ሲሰጡ ሁለት ዓይነት መንገድ የሚከተል ከመሆኑ አንጻር የሆነ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ያለ ዝርዝር የፍሬ ነገር አንቀጾች “ዝርዝሩ በመመሪያ ይወሰናል” የሚል ሀረግ የሚጠቀሙ ሲሆን ይህም የአንቀጹን ድንጋጌ ለማስፈጸም መመሪያ መውጣቱ የግድ አስፈሊጊ መሆኑን እና ይህም ወዲያውኑ ሊሆን እንደሚገባው የሚጠቁም ይሆናል፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት መመሪያው መውጣት ያለበት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ መሆን እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ተገቢው ጊዜ ይህ ሶስት ወር ይሆናል ማለት ነው፡፡
በላሊ በኩል ሁሉም አዋጆች ሊባል በሚችል ሁኔታ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች በሚለው የማጠቃለያ ክፍላቸው ሥር የአስተዳደር ተቋማት” አዋጁን ለማስፈፀም አስፈላጊውን መመሪያ ማውጣት እንደሚችል” ይደነግጋል፡፡ ይህም ተቋማቱ መመሪያ የሚያወጡት አዋጁን ለማስፈፀም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ብቻ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ይህም ማለት መመሪያውን ለማውጣትም ሆነ ላለማውጣት ውሳኔው የአስተዳደር ተቋሙ ነው፡፡ እነኚህ ሁለት አካሄዶች ባሉበት ሁኔታ መመሪያ ማውጣትን በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊፈፀም እንደሚገባው እና እንደ ግዴታ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ስለሚሆን ”በተገቢው ጊዜ” የሚል ሀረግ መጠቀም የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ መመሪያዎችን ለማውጣት እንደ ጉዳዩ ሁኔታ የተለያየ ጊዜና አቅም ስለሚጠይቅ  የተወሰነ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ የማይቻል ሆኗል፡፡
ነገር ግን የአስተዳደር ተቋማት ማውጣት የሚገባቸውን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ሳያወጡ ቀርተው ዜጎች ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት እንዳያጡ እና መብታቸው እንዳይጣበብ ረቂቅ አዋጁ ሁለት ዋስትናዎችን አስቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው በአንቀፅ 6 ሥር የተደነገገው የአስተዳደር ተቋሞች ማውጣት ያለባቸውን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ውስጥ ሳያወጡ ቢቀሩ ዜጎች ተቋማቱ መመሪያውን እንዲያወጡ መጠየቅ የሚችሉበት ሥርዓት ተመልክቷል፡፡
እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በተገልጋዮች በኩል ሲቀርብ የአስተዳደር ተቋሞች በስልሳ የሥራ ቀናት ውስጥ መመሪያ የማውጣት ሒደቱን መጀመር አልያም መመሪያውን ማውጣት እንደማያስፈልጋቸው ካመኑ ምክንያታቸውን በመግለፅ ጥያቄውን ውድቅ ማረግ ይችላሉ፡፡ መመሪያ እንዲወጣ የቀረበው ጥያቄ ውድቅ በሚሆንበት ጊዜ ውድቅ የማድረግ ውሳኔው እንደማንኛውም ውሳኔ በአዋጁ አንቀፅ 48/1/ እና 50(2) መሰረት ለፍርድ ቤት ክለሳ መቅረብ የሚችል ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሁለተኛ የአስተዳደር ተቋሞች ማውጣት የሚገባቸውን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ሳያወጡ ቀርተው ዜጎች ማግኘት የሚገባቸውን መንግስታዊ አገልግልት እንዳያጡ እና መብታቸው እንዳይጣበብ ረቂቅ አዋጁ ያስቀመጠው ዋስትና በአንቀጽ 4(2 እና 3) ሥር ተቀምጧል፡፡ ይህም የአስተዳደር ተቋማት ሊያወጡ የሚገባቸውን መመሪያ ባያወጡም እንኳን ተቋማቱ በሕግ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት ለዜጎች ሊሰጡ የሚገባቸዉን አገልግልት ወይም አስተዳደራዊ ዉሳኔ እንዲሰጡ የሚያስገድዳቸው ድንጋጌ ነው፡፡
የአዋጁ  ክፍል  ሁለት ንዑስ  ክፍል  ሁለት፤ ተቋማት መመሪያዎችን ሲያወጡ ሊከተሏቸው የሚገቡ የቅድመ መመሪያ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓትን አካቷል፡፡
በአንቀጽ ሰባት መሰረት ተቋማት መመሪያዎችን ሲያወጡ መመሪያ የማውጣቱን ሂደት ከመነሻው እስከ መድረሻው የሚገልፅ መዝገብ ማደራጀት የሚኖርባቸው ሲሆን መዝገቡ ለሕዝብ ክፍት የሚሆን ነው፡፡ የአስተዳደር ተቋማት አንድን መመሪያ የማውጣት ሂደት ሲጀምሩ ይህንኑ ለዜጎች ማስታወቅ የሚገባቸው ሲሆን ማስታወቂያው የመመሪያውን ረቂቅ ለማዘጋጀት መሰረት የሆነውን ሕጋዊ ስልጣን እና በመመሪያው ስለሚካተቱት ርዕሰ ጉዳዮች፤ ረቂቅ መመሪያውን ማግኘት ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ በረቂቅ መመሪያው ጉዳዮች  የሕዝብ አስተያየት የሚሰበሰብበትን ጊዜና ሁኔታ እንዲሁም መመሪያውን በተመለከተ የተዘጋጀውን መዝገብ ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ መግለጽ ይኖርበታል፡፡ ይህም እስከአሁን ባለን አሰራር መመሪያዎች ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ተብሎ የታመኑ ኤባለሙያዎች በጥብቅ ሚስጥርና አሳታፊ ባልሆነ ሥርዓት ሲከናወን የነበረ አሠራር በዓይነቱ የሚቀይር ነው ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በአንቀፅ 11 ሥር የአስተዳደር ተቋማት ከጉዳዮች  ከተመለከተው የቅድመ መመሪያ ማውጣት ሥነሥርዓት ነጻ የሚሆኑበትን ልዩ ሁኔታ የተቀመጠ ሲሆን ሦስት ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው የታሰቡ ሁኔታዎች ለዚህ ልዩ ሁኔታ ብቁ ያደርጋል፡፡ የመጀመሪያው አጣዳፊ ሁኔታ በመፈጠሩ ምክንያት የአስተዳደር ተቋሙ በቅድመ መመሪያ ማውጣት ሥርዓት ውስጥ ማለፍ የማይችልበት የጊዜ እጥረት ሲፈጠር ሲሆን ይህም እንደ ጤና ጥበቃና አካባቢ ጥበቃ የመሳሰሉ ተቋሞች የሚያጋጥሟቸውን አጣዳፊ ሁኔታዎች ከግምት ያስገባ ነው፡፡ ሁለተኛው ልዩ ሁኔታ ቅድመ ማስታወቂያ ማውጣቱ የሕዝብን ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ሲገኝ ሲሆን በተለይም እንደ ዋጋ ትመና ያለ አስቀድሞ ሕዝብ ቢያውቃቸው ከሚያስገኙት ጥቅም ይልቅ የሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያመዝንባቸውን የመመሪያ ዓይነቶችን ያካትታል፡፡ ሦስተኛው ሁኔታ ቅድመ ማስታወቂያ ማውጣቱ የመመሪያውን ተፈፃሚነት ፋይዳ ቢስ የሚያደርግ የሚሆንባቸውን ሁኔታዎች የሚያካትት ነው፡፡
 
ንዑስ  ክፍል  ሦስት መመሪያን ስለማፅደቅ እና ስለተፈፃሚነቱ የሚደነግግ ነው፡፡ አንቀፅ 12 በረቂቅ መመሪያው ላይ አስተያየት የመሰብሰብ እና የውይይት መድረክ ማካሄጃ ጊዜው ከማለፈ በፉት የአስተዳደር ተቋሙ መመሪያውን ማፅደቅ እንደማይችል፣ የሰበሰባቸውንም አስተያየቶች ከግምት ማስገባት እንደሚኖርበት እንዲሁም የተቀበላቸውን አስተያየቶች የማይቀበል ከሆነ የማይቀበለበትን ምክንያት በፅሁፍ ማስቀመጥ እንደሚኖርበት ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም መመሪያዎች ከመጽደቃቸው በፊት የሕጋዊነት ጉዳዮች  የሚነሳ ጥያቄ ቢኖር ለማጣራት ሲባል ወደ ፌደራል ጠቅላይ  ዐቃቤ ሕግ መላክ እንደሚኖርበት እና ጠቅላይ  ዐቃቤ ሕጉም በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ በመመሪያው ያለውን አስተያየት ካልላከ የአስተዳደር ተቋሙ የጠቅላይ ዐቃቤ ህግን አስተያት ሳይጠበቅ ሂደቱን እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡
ሌላውና በዚህ ንዑስ  ክፍል  ውስጥ የተካተተው ቁልፍ ድንጋጌ በአንቀጽ 13  ላይ የተመለከተው ሲሆን ይህም የአስተዳደር ተቋሙ በማስታወቂያ የለቀቀው  እና የመጨረሻ ሆኖ በሚወጣው መመሪያ መካከል መሠረታዊ ልዩነት መኖር እንደሌለበት የሚከለክለው ድንገጌ ነው፡፡ ይህም የአስተዳደር ተቋሙ ለሕዝብ ይፋ አድርጎ አስተያየት ከሰበሰበበት ረቂቅ መመሪያ መሰረታዊ የይዘት ለውጥ ያለው መመሪያ ቢያፀድቅ ሕዝብ የማያውቀው እና አስተያየት ያልሰጠበት ሊሆን ስለሚችል በቀደመው ረቂቅ መመሪያ  የነበረውን የህዝብ ተሳትፍ የይስሙላና ትርጉም አልባ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም የአስተዳደር ተቋሙ መሰል የይዘት ለውጥ የማድረግ መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም ህዝብን የማሳተፍ ሂደቱን እንደ አዲስ መጀመር ይኖርበታል፡፡
 
 
በዚህ ንዐስ  ክፍል  ውስጥ የአስተዳደር ተቋማት ባወጡት መመሪያ   የማብራሪያ ፅሁፍ የማዘጋጀት ግዴታ የተጣለባቸው ሲሆን መመሪያው ሲወጣ ሊኖረው ስለሚገባ ቅርጽም የተወሰኑ ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል፡፡ ስለመመሪያው የማብራሪያ ጽሁፍ መኖር መመሪያው በስራ ላይ  በማዋል ሂደት መመሪያውን ለመተርጎም ይረዳል በሚል ነው፡፡ የመመሪያው ቅርጽ በህግ ለመደንገግ የታሰበበት ምክንያት ደግሞ አሁን ባለው አሠራር የአስተዳደር ተቋማት በዚህ ረገድ ወጥነት የጎደለውና የተዘበራረቀ የመመሪያ አወጣጥ አሰራርና የመመሪያ ቅርጽ እየተከተለ ስለሆነ ይህንኑ መስመር በማስያዝ ወጥነት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡
በመቀጠል በረቂቁ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መመሪያዎቹ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሚሆኑበት ሥርዓት የተመለከተ ነው፡፡ እስከ አሁን ባለን አሠራር መመሪያዎች ማሳተም በአጠቃላይም ሆነ በነጋሪት ጋዜጣ ማሳተም በተለይ በግዴታነት የተቀመጠ ባለመሆኑ በዜጎች ክፍተኛ የመብት መጣበብ የሚፈጥሩ መመሪያዎች ሆነውም እያለ መመሪያዎቹ ለማግኘት አስቸጋሪ ናቸው፡፡ አስፈጻሚዎች ቆልፈው ይዘው ባስፈለገ ጊዜ አውጥተው የሚያስፈጽሟቸውና መልስው የሚቆልፈባቸው ናቸው፡፡ ይህም ክፍተኛ የመልካም አስተዳደር እጦት መገለጫ ከሆኑት ጉዳዮች  አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አዋጁ ከዚህ ዓይነት የጨለመ አሠራር የምንወጣበት መንገድ ለማደራጀት ሞክሯል፡፡
 
በመሆኑም መመሪያ እንደጸደቀ ወዲያውኑ ወደ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ  ተልኮ መመዝገብ ያለበት ሲሆን ዓቃቤ ሕግም በድህረ ገጹ ላይ  እንዲጭነው ግዴታ ተጥልበታል፡፡ ስለዚህ አንደኛው መመሪያውን ተደራሽ ማድረጊያ መንገድ በዓቃቤ ህግ በኩል ነው፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የመመሪያው ባለቤት የሆነው የአስተዳደር ተቋምም በዚህ ረገድ የራሱና ከፍ ያለ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በዚህም መሠረት የመመሪያው ባለቤት ለባለድርሻ አካላት አሳትሞ የማሰራጨት፤ በድህረ ገጹ መጫን እንዲሁም የመመሪያው ቅጂ ለሚፈልግ ወጪውን ሽፍኖ እንዲወስድ ሊያስችል ይገባል፡፡ መመሪያዎችም ተፈፃሚ የሚሆኑት በፌደራል ጠቅላይ  ዐቃቤ ሕግ ከተመዘገቡበት እና በተቋማቱ ድህረ ገጽ ከተጫኑበት ቀን አንስቶ ሲሆን ያልተመዘገቡ ወይም በድህረ ገጽ ያልተጫኑ መመሪያዎች ተፈፃሚነት እንደማይኖራቸው ተደንግጓል፡፡
ከአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጁ ተፈፃሚነት በፊት የአስተዳደር ተቋማት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ነባር መመሪያዎች አዋጁ በወጣ በ90 ቀናት ውስጥ ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተልከው መመዝገብ የሚኖርባቸው ሲሆን ተቋማቱም በድህረ ገጾቻቸው መጫን እና በተለያየ መልክ ለሕዝብ ተደራሽ ማደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ያልተመዘገቡ ነባር መመሪያዎች ተፈጻሚነታቸውና ህጋዊነታቸውን የሚያጡ ሲሆን የአስተዳደር ተቋማቱ የሚፈልጓቸው ከሆነ ግን በአዋጁ የተመለከተውን የመመሪያ አወጣጥ ሥነሥርዓት በመከተል እንደ አዲስ ሊወጧቸው ይችላሉ፡፡
የአስተዳደር ተቋማት ንብረቶቻቸውን በየወቅቱ የንብረት ቆጠራ እያደረጉ የሚወገደው እያስወገደ የሚጠገነውም ጠግነው በሥራ እንደሚያውሉ ሁሉ፤ መመሪያዎቻቸውንም በየጊዜው እየገመገሙ ተገቢ እርምጃ ማለትም መመሪያውን መሻር፤ መሻሻል ያለበት ሆኖ ከተገኘም ማሻሻል እንዲሁም ባለበት የመቀጠለ ጉዳይ ተገቢነቱ ከታመነበትም ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲወሰድ የታሰበው እርምጃ መሻሻል ሆኖ ከተገኘና መሻሻሉ መሠረታዊ ልዩነት በሚያመጣ ሁኔታ የሚከናወን ከሆነ ቀደም ሲል የተቀመጠው የቅድመ መመሪያ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት መከተል ይገባል ማለት ነው፡፡
 
 • ክፍል  ሦስት(አንቀጽ 20-42)
 
የአዋጁ ክፍል ሦስት የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥን የሚመለከት ሲሆን አምስት ንኡሳን ክፍሎች አካቷል፡፡ ከአንቀፅ 20 እስከ 22 የአስተዳደር ውሳኔ የሚጀመርበት ሁኔታ የተደነገገ ሲሆን የአስተዳደር ውሳኔ ጉዳዩ በሚመለከተው ሰው ጥያቄ ወይም በአስተዳደር ተቋሙ አነሳሽነት ሊጀመር ይችላል፡፡ የአስተዳደር ውሰኔ ይሰጥልኝ ጥያቄ አቤቱታ በፅሑፍ ሲቀርብ ግልፅነትን ለመፍጠርና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ቀን፣ የአቤቱታ አቅራቢው ወይም ወኪሉ ስም፣ ፊርማ እና አድራሻ፣ አስተዳደራዊ ተግበሩን የሚፈፅመው  ተቋም ስም፣ የአቤቱታ አቅራቢው መብት ወይም ጥቅም፣ ተቋሙ ሊፈፅመው የሚገባ አስተዳደራዊ ተግባር ፣ ተቋሙ ለሚተገብረው አስተዳደራዊ ተግባር መሰረት የሆኑ ምክንያቶች እና ተያያዥ ማስረጃዎችን መያዝ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ጥያቄ አቅራቢዎች በአካል ቀርበው ለሚያመለክቱ ሲሆን የአስተዳደር ተቋሞች ወጥ የሆነ ቅጽ በማዘጋጀት የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ይችላሉ፡፡ የቅጽ መዘጋጀት ለተገልጋዩም ሆነ ለአገልግልት ሰጪው ለአሠራር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡
የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ የቀረበላቸው ተቋሞች ጥያቄውን መዝግበው ጥያቄውን መቀበላቸውን የሚያረጋግጥ ደረሰኝ ለጥያቄ አቅራቢው የመስጠት ግዴታ የሚኖርባቸው ይሆናል፡፡ ጥያቄው የሚስተናገድበት ቀን ቀጠሮም በዚያን ወቅት መሰጠት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ አሁን ባለው አሠራር በብዙ አስተዳደር ተቋሞች ተገልጋዮች ለአቤቱታ ሲሄድ ማመልከቻ እንዳስገቡ እንኳ ማረጋገጫ የማያገኙበት፤ ጉዳያቸው መቼ እንደሚታይ የማያውቁበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ይህንን ተጠያቂነት የሌለበት አሠራር እንዲያበቃ የሚያደርግ ነው ተብሎ እምነት ተጥሎበታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የአስተዳደር ውሳኔ ለመስጠት የግድ አቤቱታ ወይም ጥያቄ አቅራቢ እንዲኖር አያስፈልግም፡፡ የአስተዳደር ተቋሙ በራሱ አነሳሽነት  ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚችልበት አሠራር ዝግ አይደለም፡፡ የአስተዳደር ተቋም ከፍርድ ቤት የሚለይበት አንደም ይህ ነው፡፡ ፍርድ ቤት በባለጉዳይ ከቀረበለት ጥያቄ ውጪ በራሱ አነሳሽነት ተነስቶ ውሳኔ አያሳርፍም፡፡ የአስተዳደር ተቋሞች ግን በተለይም ከጤናና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በሥልጣን ክልላቸው በሚወድቁ ጉዳዮች በራሳቸው አነሳሽነት አስተዳደራዊ ውሳኔ አስተላልፈው፤ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወስድበት ሂደት እንደተጠበቀ ነው፡፡
በክፍል ሦስት ንዑስ ክፍል ሁለት የተካተቱት የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎች ሲሆኑ መርሆዎቹ የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ፍትሓዊነትና ተገማችነት ለማረጋገጥ የተደነገጉ ናቸው፡፡ የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጥ ሰው በሕግ ሥልጣን የተሰጠው ሰው መሆን እንዳለበት ከሚደነግገው አንቀፅ 23 ጀምሮ፤ የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጥ ሰው የጥቅም ግጭትን ማስቀረት እንዳለበት፤ ሙያዊ እና በቅን ልቦና ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መስጠትም እንደሚኖርበት የሚደነግጉ አንቀፆች ተካተዋል፡፡ በተጨማሪም የአስተዳደር ውሳኔዎች የአስተዳደር ተቋሙን የስልጣን ወሰን ሊያልፉ እንደማይገባቸው፤ አግባብነት ያለውን ጉዳይ ከግምት ያስገቡ እና በምክንያት  የተመሰረቱ ሊሆኑ እንደሚገባም  ተደንግጓል፡፡ የአስተዳደር ውሳኔዎች የህዝብን እኩልነት ያከበሩ፤ በተገልጋዮች ጥቅም እና ተቋሙ በሚያስፈፅመው ሕዝባዊ ዓላማ መካከል ሚዛናዊነትን መጠበቅም የሚገባቸው እንደሆኑ ተደንግጓል፡፡ የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ ግልጽ የሆነ ሒደትን የሚከተል እና ተገማች እንዲሆንም ይጠበቅበታል፡፡ ከእነዚህ መርሆዎች አንዱንም እንኳ ሳይከተል የተሰጠ ውሳኔ ቅሬታ ሊቀርብበት እንደሚችል በቀጣይ ድንጋጌዎች የምናየው ይሆናል፡፡
 • ተቋማት የአስተዳደር ውሳኔን በተገቢው ጊዜ ውስጥ መስጠት የሚገባቸው እንደሆነ በአንቀፅ 33 የተቀመጠ ሲሆን ሁሉም የአስተዳደር ተቋማት ውሳኔዎችን ለመወሰን እንደሥራቸው ባሕሪርይ የተለያየ የጊዜ ርዝመት ሊወስድባቸው ስለሚችል አንድ ወጥ የሆነ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ተገቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ተቋሞች ውሳኔ ለሚሰጡባቸው አስተዳደራዊ አገልግልቶች የራሳቸው የጊዜ ገደብ አስቀምጠው ተገልጋዩ እንዱያውቀው ያደረጉ ስለሆነ ለእነርሱ ተገቢው ጊዜ ተደርጎ የሚወሰደው ይህ ጊዜ ይሆናል ማለት ነው፡፡
 • ተቋሞች በውሳኔ መዘግየት ምክንያት ተገልጋዮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ እንዲሁም  ተቋማቱ በተገቢው ጊዜ ባለመወሰናቸው ምክንያት በተገልጋዮች ጉዳዮች  ለሚደርሰው ጉዳት ኃላፊነት እንደሚኖርባቸው የሚደነግግ ነው፡፡ በተጨማሪም የአስተዳደር ተቋሙ ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ የማይሰጥ ከሆነ የጥያቄውን ውድቅ እንዳደረገው ተቆጥሮ ውሳኔ ጠያቂዎች ጉዲያቸውን ወደ ሚቀጥለው መፍትሔ ሰጪ አካል መውሰድ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ይህ መደረጉ አስተዳደራዊ መፍትሄ ፍለጋ ጧት ማታ በየአስተዳደር ተቋሞቹ ግቢ የሚንከራተቱ ዜጎችን ለመታደግ ያግዛል ፡፡
 •  ክፍል  ሦስት ንዑስ  ክፍል  ሦስት የአስተዳደር ውሳኔ በጽሁፍ ለተገልጋዮች መሰጠት እንደሚኖርበት በግዴታነት የተቀመጠ ሲሆን ይህም አሁን ካለው የብዙ አስተዳደር ተቋሞች አሠራር የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ የአስተዳደር ተቋማት አስተዳደራዊ ውሳኔው በቃል እንዲያውም በጸሃፊዎች  በኩል እንዲነገር እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ ረቂቅ አዋጁ እንዲህ ካለ ለመረጃ ከማይመች አሠራር ለማስወጣት ይረዳል፡፡
 •  ክፍል  አምስት በአስተዳደር ውሳኔ ላይ  የሚቀርብ ቅሬታ በራሱ በአስተዳደር ተቋሙ የቅሬታ ማስተናገጃ አካል የሚስተናገድበትን ሁኔታ የሚገዙ አንቀፆችን ይዟል፡፡ በአንቀፅ 49 እና 44 መሰረት ማንኛውም ሰው በተሰጠው አስተዳደራዊ ውሳኔ ጉዳዮች  በአስተዳደር ተቋሙ ውስጥ ቅሬታ የማቅረብ መብት ሲኖረው የአስተዳደር ተቋማትም ውሳኔው የቅሬታ ማስተናገጃ አካላትን የማቋቋም ግዳዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ ግን በአንድ በኩል ለተገልጋዮች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ቢሆንም በሌላ በኩል ግን የአስተዳደር ተቋሙም ውሳኔውን በውስጥ የአሠራር ስርዓቱ ራሱ እንዲከልስ እድል የሚሰጠው ስለሆነ ለአስተዳደር ተቋሙም ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡
 
4.  ክፍል  አራት (አንቀጽ 43-52)
የአዋጁ ክፍል አራት በፍርድ ቤት የሚደረግ የአስተዳደር መመሪያዎችና ውሳኔዎች ክለሳን የሚመለከት ነው፡፡ የአስተዳደር መመሪያዎችና ውሳኔዎች በፍርድ ቤት የሚከለሱበት ሥርዓት በሃገራችን የሕግ ሥርዓት ውስጥ በተሟላ ሁኔታ ያልነበረ ከመሆኑ አንፃር ይህ አዋጅ የአስተዳደር ጉዳዮች  የፍርድ ክለሳ ሥርዓትን (judicial review) በሀገራችን የሚያስተዋውቅ ይሆናል፡፡ የክለሳ ሥርዓት ከይግባኝ በዓይነቱ የተለየ ነው፡፡ የይግባኝ ሥርዓት የሥር ውሳኔ ሰጪ አካል መቅረብ ሳያስፈልግ ውሳኔው ተመርምሮ የሚሻር፤ የሚጸና ወይም የሚሻሻል ሲሆን ክለሳ ግን ውሳኔ ስጪው አካል የመደመጥ መብት ተጠብቆለት ውሳኔው በተወሰኑ ነጥቦች ጉዳዮች  ብቻ ተመርምሮ የሚሻር ወይም የሚጸና እንጂ ፍርድ ቤቱ የአስተዳደር ተቋሙን ተክቶ ውሳኔ ሊሰጥበት የሚቻለው አይደለም፡፡
 
 • ውሳኔ በፍርድ ቤት እንዲከለስ ሲወሰን የፍርድ ቤቶቹ አደረጃጀት ሦስት እርከኖች ያሉት በመሆኑ የሚከልሰው በየትኛው ደረጃ   ያለው ፍርድ ቤት ነው የሚለው መመለስ ያለበት ነው፡፡ የአስተዳደር ውሳኔዎች  ክለሳ የላቀ የሕግ አተረጓጎም ክህሎት እና ልምድን የሚጠይቅ በመሆኑ እና በጉዲዩ ተከሰው የሚቀርቡ የመንግሰት ተቋማትም ካሏቸው ኃሊፊነት ጋር ተመጣጣኝ በሆነ የፍርድ ቤት እርከን እንዲዳኙኙ ማድረግ ይገባል፡፡ እንያያውም ይህ ረቂቅ አዋጅ የአስተዳደር ጉዳዮችን የሚያስተናግድ ችሎት እንዲኖር ይጠይቃል፤ ይጠብቃል፡፡ በዋናነትም መመሪያ የሚሻርበት ሁኔታ መኖሩ ፍርድ ቤቱ ከተገነዘበ በተያዘው ጉዳይ  ብቻ ሳይሆን መመሪያው ሙለ በሙለ ህጋዊ ኃይል የሚያጣበት ውሳኔ እንዲሰጥ ሥልጣን የተሰጠው ስለሆነ የፍርድ ቤቱ ደረጃ ከፍ ያለ ሊሆን ይገባል፡፡
 • የአስተዳደር ጉዳይ ለክለሳ የሚቀርበው ለፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት በአስተዳደር  ጉዳዮች ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ሲሆን መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለው ውሳኔ ወደ ፌደራል ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ሰበር ችልት በሰበር የሚቀርብበት አካሄድ የተጠበቀ ነው፡፡
 • መመሪያዎች ላይ  የሚቀርብ የክለሳ አቤቱታ በማንኛውም ሰው መቅረብ የሚችል ሲሆን በአስተዳደር ውሳኔዎች ላይ  የሚቀርብ የክለሳ አቤቱታ ግን በውሳኔው ጥቅሙ በተነካበት ሰው ብቻ የሚቀርብ ይሆናል፡፡ የአስተዳደር ጉዳይ ለፍርድ ቤት ክለሳ እንዲቀርብ የሚያደርጉ ምክንያቶች ውስን እና በጥንቃቄ የተመረጡ ናቸው፡፡ የአስተዳደር ተቋማት መመሪያ በፍርድ ቤት የሚከለሰው በአዋጁ  ክፍል  ሁለት የተመለከቱትን የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች ሳይከተል የወጣ ከሆነ ወይም መመሪያው ከአስተዳደር ተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ በሆነ መልኩ ከወጣ ወይም በማናቸውም መልኩ ሕግን የሚጥስ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ሆኖም የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች ሳይከተል የወጣ መመሪያ ነው በሚል የሚቀርብ የክለሳ አቤቱታ ከሆነ አቤቱታው መቅረብ ያለበት መመሪያው በጸደቀ በዘጠና ቀናት ውስጥ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም የሕጋዊነት ችግር የሌለባቸው መመሪያዎች በሥራ ላይ   ከቆዩ በኋላ የሥነሥርዓት ድንጋጌዎችን አልተከተለም በሚል ብቻ ተፈፃሚነታቸው መስተጓጎል የለበትም ከሚል ምክንያት የመነጨ ነው፡፡
 • ውሳኔ የሚከለሰው በአዋጁ  ክፍል  ሦስት የተደነገጉትን የሥነሥርዓት እና የፍሬ ነገር መርሆዎች የጣሰ ሲሆን ነው፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ውጪ የአስተዳደር መመሪያዎች እና ውሳኔዎች በፍርድ ቤት የሚከለሱበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ነገር ግን በሌልች ልዩ ሕጎች የአስተዳደር ተቋማት እና አስተዳደራዊ የዳኝነት  አካላት የሰጧቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች ወደ ተለያዩ የፍርድ ቤት እርከኖች በይግባኝ የሚቀርቡበት አካሄድ እንደተጠበቀ ነው፡፡
 • ውሳኔ ለፍርድ ቤት ክለሳ የሚቀርበው ውሳኔው የመጨረሻ ከሆነና አስተዳደራዊ መፍትሔዎችን አሟጦ ከጨረሰ በኋላ ነው የሚሉ ድንጋጌዎች ተካትተዋል፡፡ ነገር ግን አስተዳደራዊ መፍትሄ የመስጠቱን ሂደት ከሚገባው ጊዜ በላይ   የተራዘመ እንደሆነ ተገልጋዮች አስተዳደራዊ መፍትሄን አሟጦ መጨረስ ግዴታ ሳይኖርባቸው ጉዳዩን ለክለሳ ማቅረብ ይችላ፡፡ የአስተዳደር ጉዳዮች  ለፍርድ ቤት ለክለሳ የሚቀርቡበት ጊዜ እንደየሁኔታው የተለያየ ነው፡፡ የአስተዳደር ውሳኔ በፍርድ ቤት እንዲከለስ የሚቀርብ አቤቱታ ባለጉዳዩ ውሳኔውን እንዲያውቀው ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የ30 ቀናት ጊዜ ውስጥ ለፍርድ ቤት መቅረብ ይኖርበታል፡፡ የአስተዳደር ተቋሙ ያወጣው መመሪያ ከአስተዳደር ተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ ነው በሚል ወይም ሕግን የሚጥስ በመሆኑ ምክንያት የሚቀርብ የክለሳ አቤቱታ በማንኛውም ጊዜ መቅረብ የሚችል ሲሆን ይህም ማንኛውም ያገባኛል የሚል ሰው በማንኛውም ጊዜ የመመሪያዎችን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት እንዲቃወም እድል የሚሰጥ ነው፡፡
 • አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ አስፈሊጊ ሆኖ ካገኘው አቤቱታው የቀረበበት የአስተዳደር ተቋም በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ የፅሁፍ መልስ እንዲሰጥ ሊያዝ ይችሊል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ የተቋሙን መልስ ሳይጠብቅ አቤቱታውን ውድቅ ማድረግ የሚችል ይሆናል፡፡ በላላ በኩል ግን ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን መመርመር ያለበት ሆኖ ካገኘው የአስተዳደር ተቋሙ መልስ እንዲሰጥ እድል ሊሰጠው ይገባል እንጂ የአስተዳደር ተቋሙ ሃሳብ ሳይቀበል የአስተዳደር ውሳኔሊሽር አይገባም፡፡ አቤቱታው መመርመር ያለበት ሆኖ ሲገኝ ተቋሙ የቀረበበትን አቤቱታ በተመለከተ አስፈላጊ ሰነዶችን የማቅረብ ግዴታ የሚኖርበት ይሆናል፡፡
 • ውሳኔ አሰጣጥ እና አፈጻጸምን በሚመለከቱ ድንጋጌዎች በአዋጁ  ክፍል  አራት ንዑስ  ክፍል  አራት ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቱ የክለሳ አቤቱታውን በአጭር ጊዜ መርምሮ ውሳኔ መስጠት የሚኖርበት ሲሆን በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ውሳኔውን እንዲሰጥ ጊዜ ቆርጦ ግዴታ መጣል ተገቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ምክንያቱም ካለው የፍርድ ቤቶች የሥራ ጫና አንጻር በዚህ ጊዜ ውስጥ ተወስኖ ይጠናቀቅ ተብል በአዋጅ ቢቀመጥ እና  ፍርድ ቤቱም ባለው ጫና ምክንያት ያ ጊዜ ካለፈ በኋላ የተሰጠ ውሳኔ ህገ ወጥ ሊሆን ነው ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው፡፡
 • 56 መሰረት ፍርድ ቤቱ የክለሳ አቤቱታ የቀረበበትን መመሪያ ወይም የአስተዳደር ውሳኔ የማፅናት፣ በሙለ ወይም በከፊል የመሻር ሥልጣን ሲኖረው የአስተዳደር ውሳኔዎችን ተክቶ ውሳኔ የመስጠት ወይም የመሻሻል ሥልጣን ግን አይኖረውም፡፡ ይህም የተደረገው የአስፈጻሚው አካልና ዳኝነት አካሉ ህገ መንግስታዊ የሥራ ድርሻ ተከብሮ እንዲቀጥል ለማስቻል  ነው፡፡ በመሆኑም የአስተዳደር መመሪያም ሆነ ውሳኔ በሙሉ ወይም በከፊል በፍርድ ቤት በሚሻርበት ወቅት የአስተዳደር ተቋማቱ ራሳቸው በፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተጠቆሙ ግድፈቶችን የማስተካከል እና የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች ተከትለው እንደገና የመስራት ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡
 • የሚያሳየው ፍርድ ቤት የአስተዳደር ተቋማትን አሰራር ሕጋዊነት የመቆጣጠር እንጂ እነርሱን ተክቶ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን እንደሌለው የሚያስገነዝብ ነው፡፡
 
5.  ክፍል  አምስት፤ የማጠቃለያ ድንጋጌዎች (አንቀጽ 58-62)
የአዋጁ ክፍል አምስት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን በአንቀፅ 58 ጉዳዮች በፍርድ ቤት የሚደረገው የአስተዳደር ጉዳዮች  የክለሳ ሥነሥርዓት ጉዳዮች  ባልተመለከቱ ሁኔታዎች ጉ  የፍትሀብሄር ሥነሥርዓት ሕግ ተፈፃሚነት እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡ ይህም በአዋጁ ክፍል አራት ንዐስ  ክፍል  ሦስት እና አራት የተቀመጡት ድንጋጌዎች ምልእነት የሌላቸው በመሆኑ ክፍተታቸው በፍትሀብሄር ሥነሥርዓት ሕጉ እንዲሟላ የማድረግ ዓላማ ያለው ድንጋጌ ነው፡፡
 • ተቋማት መመሪያ በማውጣትም ሆነ የአስተዳደር ውሳኔ በመወሰን ረገድ በፈጸሙት ጥፋት ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም ሰው የአስተዳደር ተቋሙ የጉዳት ካሳ እንዲከፈለው መጠየቅ እንደሚችል በአንቀፅ 59 መሰረት የተደነገገ ሲሆን ይህም የአስተዳደር ተቋማትን የተጠያቂነት ደረጃ ከፍ ለመድረግ የተቀመጠ ድንጋጌ ነው፡፡ ሆኖም የጉዳት ካሳ አከፋፈል ተገቢ በሆነው ሕግ በተለይም ከውል ውጪ በሚደርስ ኃላፉነት አግባብ ያላቸው ድንጋጌዎች መሰረት የሚፈፀም እንጂ ይህ የአስተዳደር ሥነ ስርዓት ልዩ የካሳ አከፊፈል ሥርዓት የሚደነግግ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡
 • ተቋማት ኃላፊነታቸውን በሚወጡበት ጊዜ በሌላ የአስተዳደር ተቋም የሚገኝን መረጃ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ስለሚችል እና ይህ በማይሆን ጊዜ ተጎጂ የሚሆኑት ተገልጋዮች በመሆናቸው የአስተዳደር ተቋማት እርስ በእርሳቸው መረጃ የመለዋወጥ ግዴታ እንዲኖራቸው በአዋጁ አንቀፅ 60 ተደንግጓል፡፡ ሆኖም የመረጃ ነጻነት እና ሚስጥራዊ መረጃን በተመለከተ ያሉ ሌሎችች ሕጎች ተፈጻሚነታቸው የተጠበቀ ነው፡፡
is it still on draft stage?
i couldnt know wether it has been appoved or not as the 2012 E.C list of approved laws are not on the webicte. 

Vote