Participate

የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

 የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና  የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  አጭር ማብራሪያ
       
1)የአዋጁ አስፈላጊነት እና አላማኮቪድ-19  ክትባትም ሆነ መድሃኒት የሌለው፣ በፍጥነት የሚዛመት እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሰብዐዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እያስከተለ የሚገኝ ዓለም ዓቀፍ ወረርሽኝ እንደሆነ ይታወቃል። የቫይረሱ ስርጭት በተለያዩ ሃገራት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እያጠቃ ሲሆን፣ ለብዙ ሺዎች መሞትም ምክንያት ሆኗል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር በተለመደው የጤና አጠባበቅ ዘዴ እና አካሄድ የዜጎችን ደህንንነት ማስጠበቅ አዳጋች በመሆኑ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት ሃገራት የሰዎችን እንቅስቃሴ ከመገደብ ጀምሮ ሌሎች በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። እነዚህ እርምጃዎች በመደበኛው ጊዜ ዕይታ ሲመዘኑ ከፍተኛ የመብት ጥሰት የሚመስሉ ቢሆኑም እነዚህ የመብት እገዳዎች ተግባራዊ ካልተደረጉ ሕዝብ እና ሃገር ከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃሉ። ስለዚህ ከባድ የሆነውን አደጋ ለመቋቋም እና ሕዝብ እና ሃገርን እጅግ ከከፋ ጥፋት ለመታደግ በልዩ ሁኔታ መብቶች እና ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ላይ እገዳ ማድረግ እና አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። በዚህም መሰረት በርካታ ሃገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የወረርሽኙን ጥቃት እና ጉዳት ለመከላከል እየሰሩ ይገኛሉ። በሃገራችን ተጨባች ሁኔታም ቫይረሱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን እያስከተለ የሚገኝ ሲሆን ለነዚህ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኖዋል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሚተዳደርበትን ሥርዓት በአንቀጽ 93 ላይ አስቀምጧል። በአንቀጽ 93 (1) (ሀ) መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መነሻ ከሚሆኑ ሁኔታዎች አንዱ “የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት” የሚል ነው። የኮቪድ-19  የሕዝብን ጤንነት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ እንደሆነ ዕሙን ነው። ይህን ወረርሽኝ  ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳለጥ እና ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ከተለመደው አሠራር እና ሕገ-መንግሥታዊ ማዕቀፍ ወጥቶ በልዩ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይጠይቃል። ለምሳሌ፡- ለማኅበራዊ፣ ኃይማኖታዊ ወይም ፖለቲካዊ ዓላማ ዜጎች የመሰባሰብ ሕገ-መንግሥታዊ መብት አላቸው። ይህን መብት በመጠቀም የሚደረጉ ስብሰባዎች ግን የኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰራጭ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ፣ ለዜጎች ጤንነትና ደህንነት አደጋ ስለሚሆኑ እነዚህን ዓይነት ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ መከልከል ያስፈልጋል። ይህን አይነት ክልከላ ደግሞ ሕገ-መንግሥታዊ መብቶችን ማገድ በመሆኑ እንዲህ ያለው ሰፋ ያለ የመብት እገዳ በሕገ-መንግሥቱ ተቀባይነት የሚኖረው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ነው። ለዚህም ነው ብዙ ሃገራት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ለማጠናከር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያውጁት። በሃገራችን ኢትዮጵያም የኮቪድ-19 የኮሮናሥርጭትን ለመከላከል፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ የተለያዩ እክሎችን በተሻለ መንገድ ለመወጣት ይቻል ዘንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኗል። አዋጁ መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን በሚወስድበት ጊዜ የተሻለ ነጻነት እና አቅም እንዲኖረው፣ የመንግስት ሥልጣን ላይ ያሉ ገደቦች ወይም የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች በተለየ ሁኔታ ለጊዜው ተፈጻሚነታቸው ቀርቶ በሙሉ ኃይል፣ በተቀላጠፈ እና በተቀናጀ መልኩ ለወረርሽኙ ምላሽ መስጠት እንዲቻል በማሰብ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተዘጋጅቷል።
ወረርሽኙን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳለጥ እና ከሕግ አንጻር አስቻይ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ፤ የዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አላማ፣ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ ተግዳሮቶችን በተመለከተ አስፈላጊውን እርምጃዎች የመደንገግ ስልጣን ለስራ አስፈጻሚው የመንግስት አካል መስጠት ነው። ከእነዚህ ተጓዳኝ ተግዳሮቶች በቀጥታ የኮቪድ-19 ከሚያስከትለው የጤና ችግር ባለፈ የሚከሰቱ የፀጥታ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ናቸው። የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ባለፈ እነዚህን ተጓዳኝ ተግዳሮቶች ለመወጣት መንግስት ከወትሮው የላቀ ስልጣን እና ህጋዊ አቅም እንዲኖረው ማድረግ የዚህ አዋጅ አንዱ አላማ ነው። ሊያጋጥም የሚችልን የሰላም እና የፀጥታ መደፍረስ፣ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ እና ማህበራዊ ውጥንቅጥ ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር፣ እንዲህ ያለ ችግር ካጋጠመም ከተለመደው አካሄድ ወጣ ባለ መልኩ ተጨማሪ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ይሆናል። ይህን ለማድረግ አስቻይ የሆነ የህግ ሁኔታ መፍጠር የአዋጁ አንዱ አላማ ነው። አዋጁ እነዚህን አላማዎች ይዞ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት  77 (10) እና 93 መሠረት የሚታወጅ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው። በመሆኑም   ይህ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀ በኋላ፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት  በሕገ መንግስቱ 55(8) እና 93(2) መሰረት ቀርቦ እንደሚጽድቅ ይጠበቃል። ስለዚህ ይህ ረቂቅ አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካጸደቀው ሰአት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን የሚያሳይ ተጨማሪ የማጽደቂያ አዋጅ ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መታወጅ ይኖርበታል። የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የማጽደቂያ አዋጅ በሚያውጅበት ወቅት አብሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93(5) መሰረት ያቋቁማል።
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93(1) (ሀ) እና (ለ) በግልጽ እንደተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፌደራል መንግስቱ እና በክልል መስተዳደሮች ሊታወጅ ይችላል። አንቀጽ 93(1) (ለ) ታሳቢ የሚያደርገው ሃገር አቀፍ ያልሆኑ፣ በተለይም በአንድ ክልል ውስጥ የተፈጥሮ አደጋ ወይም የህዝብን ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል በሽታዎችን ሲሆን፤ እንዲህ ያለ አደጋ ወይም በሽታ ሲያጋጥም በሃገር አቀፍ አዋጅ ሳይሆን ክልሎች እንደየራሳቸው ተጨባች ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ   እንደሚችሉ ከዚህ የሕገመንግስት አንቀጽ መረዳት ይቻላል። ኮቪድ-19 ከሃገር አቀፍ አልፎ አለም አቀፍ ወረርሽን በመሆኑ፣ እንደሃገር የተቀናጀ እና የተሳለጥ የመከላከል፣ የመቆጣጠር እርምጃዎችን ለመውሰድ በአንቀጽ 93(1)  (ሀ)  መሰረት ሃገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ተገቢ ነው።
2) የአዋጁ ይዘትየአዋጁ አንኳር ይዘት በአዋጁ አንቀጽ 4(1) የተለፀው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወረርሽኙ ሥርጭት እያስከተለ ያለውንና ሊያስከትል የሚችለውን ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ለመቀነስ እና ለመከላከል ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚያወጣቸው ደንቦች የመብት እገዳዎችንና፣ እርምጃዎችን  በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (4) (ሀ) መሰረት ለመደንገግ የተሰጠው ስልጣን ነው። ይህም ማለት የወረርሽኙ ሥርጭት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ወይም ለመከላከል እንደሁኔታው እና እንደአስፈላጊነቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማወጣት የመብት እገዳዎችን ማድረግ እና እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል። የመብት እገዳዎች ሲባል፣ በሕገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተዘረዘሩትን መብቶች ተፈጻሚነት ወይም ህጋዊ ወጤት እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው። እርምጃዎችን መውሰድ ሲባል ድግሞ መብቶችን ከማገድ ጋር ቀጥተኛም ሆን ተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው እና  ውሳኔዎች፣ አተዳደራዊ እርምጃዎች ወይም የሚሰጡ መመሪያዎች ወይም አቅጣጫዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
 እነዚህን የመብት ገደቦች እና እርምጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወስጥ ዘርዝሮ ማስቀመጥ ያልተቻለው አስፈላጊ የሚሆኑት ገደቦች እና እርምጃዎች ከጊዜ ጊዜ እና በሃገሪቱ ውስጥ ከቦታ ቦታም ሊለያዩ ስለሚችሉ ነው። እንደወረርሽኙ ስርጭት የስፋት አድማስ፣ እንደሚያስከትለው ጉዳት አስፈላጊ የሆኑት ገደቦች እና እርምጃዎች ሊለዋወጡ ይችላሉ። አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ ውስጥ ሁሉ የሚያስፈልጉት ክልከላዎች እና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ተለዋዋጭነት ሊኖራቸው ስለሚችል፣ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት፣ በየጊዜው ያለውን ሁኔታ በመገምገም እና ስለቫይረሱ ስርጭትም ሆነ ባህሪ የሚገኙ ሳይንሳዊ መረጃዎችን፣ የህዝብ ጤና ባለሞያዎችን ምክር ከግምት በማስገባት የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስልፈጋል።  ይህን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ዝርዝር እና ቋሚ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን ከመዘርዘር ይልቅ እንዳስፈላጊነቱ  ተለዋዋጭ (flexible) በሆነ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን እንዲደነግግ አዋጁ ስልጣን ይሰጠዋል።  አዋጁ በዚህ መልክ የተቀረፀው አስፈላጊ የሆኑ የመብት እገዳዎች እና እርምጃዎች ዝርዝር ሁኔታ ከጊዜ ጊዜ፣ ከቦታ ቦታ ሊለዋወጥ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ ፣ ተጨባጭ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት፣ አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ የሆነ እገዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ነው። ይህ አይነት አካሄድ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች የተሻለ ውጤታማ እንዲሆኑ እና በሕገ-መንግሥታዊ መብቶችም ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አስፈላጊ ከሆነው መጠን ያላለፈ እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል። በደፈናው ከሚጣሉ ገደቦች ይልቅ፣ በየጊዜው ያለውን ሁኔታ እና ስጋት ከግምት በማስገባት፣ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እንዲህ ያለ ማዕቀፍ ተመራጭ ነው።
ሆኖም በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 4(1) ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰጠው የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን የመደንገግ ስልጣን ገደብ የለሽ የሆነ ስልጣን አይደለም። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚያወጣቸው ደንቦችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማንኛውም ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (4) (ሐ) ልዩ ጥበቃ የተደረገላቸውን ድንጋጌዎች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታውጅበትን ስልጣን እና ስርዐት የዘረጋው ሕገ መንግስት፣ በአንቀጽ 93 (4) (ሐ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውድ ውስጥ እንኳን ቢሆን ሊታገዱ የማይችሉ ሕገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን በግልጽ ዘርዝሮዋል። እነዚህም በሕገመንግስቱ አንቀጽ 1 የተቀመጠው የመንግስት ስያሜ፣ በአንቀጽ 18 የተቀመጠው የኢሰብዐዊ አያያዝ መከልከል፣ በአንቀጽ 25 የተቀመጠው የእኩልነት መብት እና በአንቀጽ 39(1) እና (2) የተካተተው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መብቶች ናቸው። የረቂቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁም አንቀጽ 4(2) 2)        የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚያወጣቸው ደንቦችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማንኛውም ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (4) (ሐ) ልዩ ጥበቃ የተደረገላቸውን ድንጋጌዎች የሚገድቡ ሊሆኑ እንደማይችሉ በመግለጽ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስልጣን ላይ ያለውን ገደብ እና የሕገመንግስቱን አንቀጽ 93 (4) (ሐ)ን ያጸናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዋጁ በግልጽ ባይካተተምም፣ በአለም አቀፍ ህግ እና  አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ  በተለመደው አሰራር መሰረት ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው የ “አስፈላጊነት” እና “ተመጣጣኝነት”  መርሆዎችም  የሚንስትሮች ምክር ቤትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስልጣን የሚገድቡ አጠቅላይ መርህዎች ተደርገው በታሳቢነት የሚወሰዱ ናቸው። 
ረቂቅ አዋጁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነትን በተመለከት  የመብት እገዳዎቹና እርምጃዎቹ ዝርዝር ሁኔታ በየጊዜው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለዚሁ ዓላማ በሚያቋቁመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እየተወሰነ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ረቂቁ ያመላክታል። ይህም ማለት የሚንስትሮች ምክርቤት በደንብ የሚደነግጋቸውን የመብት እገዳዎች እና እርምጃዎች ዝርዝር ሁኔታ የመወሰንን ስልጣን ራሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊሰራበት ይችላል ወይም እንዳስፈላጊነቱ ለዚሁ አላማ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሊያቋቁም ይችላል። ስለዚህ ሙሉው የሚንስትሮች ምክር ቤት ሳይሆን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሃላፊነቱን በውክልና የሰጠው የሚኒስትሮች ኮሚቴ የመብት እገዳዎቹና እርምጃዎቹ ዝርዝር ሁኔታ ወስኖ ለህዝብ ይፋ የማድረግ ስልጣን ይኖረዋል።
ረቂቅ አዋጁ ማንኛውም ሰው በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ሌላ በሕግ ሥልጣን ባለው አካል የሚሠጥ ሕጋዊ ትዕዛዝ እና መመሪያን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።  እንዲሁም የፌደራል፣ የክልል የሕግ አስከባሪ ተቋማት እና ሌሎች በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት  ተመጣጣኝ ኃይል በመጠቀም በረቂቅ አዋጁ  አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ይፋ የተደረጉ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን  የማስፈጸም ስልጣን እንደሚኖራቸው ይደነግጋል። ይህም የማስፈጸም ስልጣን በሚኒስትሮች ምክርቤት ቤት በሚወጣው ደንብ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውክልና በሚሰጠው ኮሚቴ በሚወጡ መመሪያዎች በሚደነገገው አግባብ የሚተገበር ይሆናል።
የረቂቁ አንቀጽ 6 በወንጀል ሕግ የተካተቱ አግባብነት ያላቸው የወንጀል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን፣ የተሰጠ መመሪያ ወይም ትዕዛዝን ሆን ብሎ የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ያስቀምጣል። ስለዚህ አንድ ሰው ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ሌላ ሰው በቫይረሱ እንዲያዝ ያደረገ ቢሆን ይህን በተመለከተ በወንጀል ህጉ በተቀመጡት የወንጀል ድንጋጌዎች መሰረት ተጠያቂ ይሆናል። ነገር ግን በወንጀል ህጉ ወይም ሌሎች አግባብነት ባላቸው ህጎች ያልተሸፈኑ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን የሚጥሱ ሰዎችን ተጥያቂነት በተመለከተ ደግሞ የረቂቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ  6(1) ተፈጻሚ ይሆናል። ይህንንም ተፈጻሚ የማድረግ ሃላፊነት ለፌደራል እና ለክልል ጠቅላይ አቃቤ ህጎች አዋጁ ይሰጣል። የአዋጁ አላማ የተሳካ እንዲሆን እና ማንም ሰው ክልከላውን ቀድሞ ለማወቅ እድል ሳይኖረው ክልከላውን በመጣስ ተጠያቂ እንዳይሆን ደግሞ የረቂቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ 7 በአቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የሚደነገጉ የመብት እገዳዎችና እርምጃዎች ዝርዝር ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እና ሕግ የማስረፅ ሃላፊነት በተጣለበት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በስፋት ለሕዝብ ተደራሽ በሆኑ የመገናኛ ብዙሃን መገለጽ እንዳለባቸው ይደነግጋል። የፌደራልም ሆነ የክልል፣ እንዲሁም የግል ሚድያዎች ከዚህ ጋር የሚሰጡ ማብራሪያ እና ገለጻዎችን በተለያዩ ቁንቋዎች ለህዝብ የማድረስ ሃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው።  አዋጁ በመላው ሃገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአምስት ወራት ተፈጻሚ ይሆናል። ይህ የሆነበት ምክኛት በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የወረርሽኙን ስጋት ልንቆጣጠረው እንችላለን በሚል እሳቤ ነው። በኢፌድሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 93(3) መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅበት የሚችልበት የጊዜ ጣራ ስድስት ወር ሲሆን፣  ይህ ረቂቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ለአምስት ወራት ነው።  ሆኖም እንደአስፈላጊነቱ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አምስት ወር ሳይሞላው ቀድሞ ሊነሳ የሚችልበት ወይም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93(3) ሊታደስ የሚችልበት አግባባም እንደተጠበቀ ነው። በተጨማሪም በሕገመንግስቱ አንቀጽ 93(5) እና (6) መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አውጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ እንደሚያቁቁም የተደነገገ በመሆኑ በዚህ አዋጅ ውስጥ ማካተት ሳያስፈልግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህን አዋጅ ለማጽደቅ በሚያወጣው የማጽደቂያ አዋጅ እንደሚካተት ይታመናል።
 
 
 
 
 
 
 

Vote