Participate

የፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ

የጥብቅና ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ የተዘጋጀ ማብራርያ
መግቢያ
በአንድ ሀገር ዉስጥ በሚደረግ የፍትህ አስተዳደር ስራ ዉስጥ ጠበቆች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመሳተፍ ፍትህ እና የህግ የበላይነት ተከብሮ የሚኖርባት ሀገር እውን በማድረግ  ሂደት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ አካላት እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ይኸዉም የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብት እና የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት አንደኛዉ መንገድ ፍትህን የሚሹ ዜጎች በጠበቆች ወይም ጥብቅና ድርጅቶች ተገቢዉን የህግ ምክር ሲያገኙ እና በአግባቡ ሲወከሉ ነው፡፡ በመሆኑም በሀገራችን የህግ የበላይነት እና የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብትን በማረጋገጥ ሂደት ጠበቆች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል በፌደራል ደረጃ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፍቃድ አሰጣጥ እና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 199/1992 የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች የስነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 57/1992 እና የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 65/1992 እንዲሁም በክልሎችም ተመሳሳይ ህጎች ወጥተዉ እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡
ይሁንና በእነዚህ ህጎች መሰረት በሚሰጠዉ የጥብቅና ሙያ አገልግሎት ላይ ሰፋ ያለ የህግ እና የአሰራር፤ እንዲሁም ከጠበቆች ብቃት እና ሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑን በተቋማችን በተደረገዉ ሀገር አቀፍ ጥናት ለማወቅ እና ለመለየት ተችሏል፡፡  ከተለዩትም ችግሮች መካከል ነጻ የጥብቅና አገልግሎት በአግባቡ መለካት የሚስችል መለኪያ አለመቀመጡ፣  ባልታደሰ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ጠበቆች መቆጣጠር የሚቻልበት አሰራር አለመቀመጡ፤ ፍቃድ አለማሳደስ በቀጥታ የዲሲፕሊን ጥፋት ከመደረጉ በፊት ሌሎች አማራጮች አለመቀመጣቸዉ፤ የጠበቆች ዲሲፕሊን ጉባኤ ገለልተኛ አለመሆን እና ለጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ የዉሳኔ ሀሳብ ከማቅረብ ባለፈ በራሱ ዉሳኔ የማይሰጥ መሆኑ፤ በዲሲፕሊን ጉዳይ ይርጋ፤ ደጋጋሚነት እና መሰየምን  የመሳሳሉ ሀሳቦች ያልተካተቱ መሆኑ፤ በህግ መሰረት ጉዳይ አጣርተዉ በማይዙ ተገቢዉን ክርክር በማያደርጉ፣ ምስክር እና ተከሳሽ በሚያስጠፉ፣ ደንበኛ እና ተከራካሪ ወገንን ባከበረ መልኩ ክርክር  በማያደረጉ እና ሌሎች የስነ-ምግባር ጉድለት ባለባቸዉ ጠበቆች ላይ ተገቢዉን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ ተመጣጣኝ የዲሲፕሊን ቅጣት እንዲቀጡ አለማድረግ ዋና ዋናዎቹ በጥብቅና አገልግሎቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ናቸዉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሚሰጠዉ የጥብቅና ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመንግስት (ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ) ቁጥጥር ስር መሆኑ አገልግሎቱ በሚጠበቅበት ደረጃ እንዳያድግ እና የሙያ ነጻነቱን በአግባቡ በጠበቀ መልኩ እንዳይሄድ ክፍተት ያለ በመሆኑ፤ እንዲሁም በስራ ላይ ያሉት የጥብቅና ህጎች ሀገሪቱ ካለችበት አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አንጻር ሊኖሯት የሚያስፈልጉ የጥብቅና ድርጅቶችን በተደራጀ ሁኔታ የሚመሩ አለመሆናቸዉ፤ እንዲሁም ከጠበቆች ዲሲፕሊን ክስ እና ቅጣት አንጻር ይርጋ፣ ደጋጋሚነት፣ መሰየም የመሳሰሉ ጉዳዮችን የሚዳስሱ አለመሆናቸዉ  በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ክፍተት ፈጥሯል፡፡
በመሆኑም እነዚህን እና ሌሎች በጥናት ሰነዱ የተለዩ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል፣ የጥብቅና አገልግሎት አሰጣጥ እና አስተዳደር ስርዐቱን ዉጤታማ በማድረግ የጠበቆችን መብት እና ነጻነት ባስጠበቀ መልኩ የተገልጋዮችን መብት ለማስከበር እና ብሎም ጠበቆች ትክክለኛ የፍትህ ባለድርሻ አካል ሆነዉ እንዲሰሩ ለማስቻል እና በሌሎች በረቂቅ አዋጁ መግቢያ ላይ በተጠቀሱ ምክያቶች ይህንን አዋጅ ማርቀቅ አስፈልጓል፡፡ ​​​​​​​
NB
ረቂቅ አዋጁ ላይ ማንኛውንም አስተያየት ወይም ጥያቄ ካሎት በአ-ሜይል አድራሻ (info@hopr.gov.et) ብትልኩልን የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በማየት እንደ ግብዓት የምጠቀም መሆኑን እንገልጻለን::   

Vote