News News

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በዋና ኦዲተር በተገኘበትን የኦዲት ግኝቶች ላይ አፋጣኝ የእርምት ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበት ተገለጸ

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በዋና ኦዲተር በተገኘበትን የኦዲት ግኝቶች ላይ አፋጣኝ የእርምት ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበት ተገለጸ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የቋሙን የኦዲት ግኝት፣ የበጀት አጠቃቀምና የንብረት አወጋገድ ስርዓቱን በተመለከተ ባደረገው የመስከ ምልከታ ወቅት ከ24 የማያንሱ የተለያዩ የኦዲት ግኝቶች መኖራቸውን አረጋግጧል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በተዘዋዋሪ፣ በገቢና ወጪ፣ በተከፋይና ተሰብሳቢ ሂሳቦች በዋናነት እንደሚጠቀሱ ተገልጿል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው ወቅት የኦዲት ግኝት የታየባቸው ሪፖርቶች በመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቀሚ ኮሚቴ የፋይናንስ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን ለተቋሙ አመራሮች ግብረ መልስ በሰጡበት ወቅት የጥሬ ገንዘብና የካዝና ቆጠራ መደረጉን፣ አለአግባብ የተመዘገበ ገንዘብ አለመኖሩን፣ የነዳጅ ልኬታ መኖሩን እና የባንክ ማስታረቂያ ስራውን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይም የስልክ ወጪን አስመልክቶ ደንብና መመሪያውን ጠብቆ ባለመሰራቱ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን፣ ከመምህራንና ከአስተዳደሩ ሰራተኞች ከ152 ሺህ ብር በላይ ለተቋሙ ተመላሽ መደረጉን፣ እንዲሆም ለሾፌሮችና ለሰራተኞች ያለአግባብ ይከፈል የነበረው የትርፍ ሰዓት ክፍያ መቋረጡንም በአወንታዊ የታዩ መልካም ስራዎች እንደሆኑ እና የተቋሙን የቢሮ አደረጃጀቱንም በጥሩ ጎን አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩልም የሰለጠነ የሰው ሀይል ውስንነት መኖሩን፣ በንብረት አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ዙሪያ እና የህጻናት ማቆያ ግንባታ አለመጀመሩን በክፍተት አመላክተዋል፡፡

በተመሳሳይም በግዥ ስርዓቱ ላይ የአሰራር ስርዓት እና ተመን ያልወጣላቸው ስራዎችን የሚያስከትሉትን አሉታዊ ጫና ለመቅረፍ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን፣ በወጪ ቀሪ ሂሳቦች፣ ከተማሪ ማበረታቻ እና ከኮማንድ ፖስት ጋር በተየያዘ እጥረቶች እንዳሉ  ጠቁመዋል፡፡

የተቋሙ የውስጥ ኦዲት ደንብና መመሪያን ተከትሎ ተጨባጭ ስራ ለመስራት የበለጠ መጠናከር እንዳለበት፣ ተመን ያልወጣላቸው እና ለአሰራር እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች ከሚመለከተው አካል ጋር በመተባበር አንዲፈቱ ማድረግ እና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮችን በተመለከተ መሰራት ያለባቸው ስራዎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኑርልኝ ተፈራ በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው ግብረ መልስ እንደ ግብዓት ወስደው የሚያስተካክሏቸው በርካታ ስራዎች እንዳሉ ገልጸው ተመን ባልወጣላቸው የአሰራር ስርዓቶች ላይ ከተከበረው ምክር ቤት እና ከሚመለከታቸው አካላት እገዛ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩልም ተቋሙ የበጀት እጥረት ስለገጠመው በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ የህንጻ ግንባታዎች ስራ መቋረጡን ገልጸው የህጻናት ማቆያን በተመለከተ ቦታውን መርጠው በቀጣይ አመት ግንባታ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡