News News

በኢትዮ-ሶማሌ ክልል የሚካሄደው የኮንትሮባንድ ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ

በኢትዮ-ሶማሌ ክልል የሚካሄደው የኮንትሮባንድ ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን በኢትዮ-ሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማና በቶጎ ውጫሌ ባደረገው የመስክ ምልከታ የኢንቨስትመንቱን እና የንግዱን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን የኮንትርባንድ ንግዱን ለመግታት ጥረት ቢደረግም ችግሩ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን ተገዝቧል፡፡

አማደሌ የቁም እንሰሳት ማቆያ ጣቢያ ኳራንታይን ግንባታው ከ10 ዓመት በፊት ቢጀመርም በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ተጠናቆ ስራ ሊገባ ባለመቻሉ ህገወጥ የቁም እንሰሳት ግብይት እንዲባባስ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የቋሚ ኮሚቴው ቡድን ተረድቷል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ የኮንትሮባንድ ንግድ የሚካሄድ ሲሆን በእንሰሳት ዘርፍ በየቀኑ በአማካኝ አስከ 1000 ግመሎች እና ከ600 በላይ ፍየሎች በገፍ ወደ ጎረቤት አገሮች እንደሚላኩና አገሪቱ ከእንሰሳት ዘርፍ ማግኘት የነበረባትን ሀብት እያጣች መሆኑን ቡድኑ አረጋግጧል፡፡

በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሀብቶች በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በቂ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ባለመኖሩ ምክንያት የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ነው ቡድኑ የተገነዘበው፡፡

ቡድኑ በጂግጂጋ ከተማ የሚገኙትን ሆፕ ፈሎር እና ሊበን የዱቄት ፋብሪካዎች በስንዴ አቅርቦት፣ በመብራት መቆራረጥ እና በሰላም እጦት ምክንያት ማምረት ከሚገባቸው በታች እያመረቱ እንደሆነ ተረድቷል፡፡

የክልሉ አመራሮች በበኩላቸው ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በንግዱም ሆነ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ አመርቂ ውጤት እንዳልታየ እና ባለሀብቶችም በጸጥታ ምክንያት ወደ ክልል ገብትው ኢንቨት ለማድረግ ተቸግረው እንደነበር ገልጸዋል፡፡  

የክልሉ የንግድ፣ትራንስፖርትና ኢንዱስትሪ ንግድ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ከድር አብዲረህማን በበኩላቸው የክልሉ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በቀድሞው በአብዲ ኢሌ አስተዳድር ስርዓት ተሸመድምዶ እንደነበር ገልጸው አዲሱ የለውጥ ሀይል ተደራጅቶ ወደ ስራ ከከባ ወዲህ ተስፋ ሰጪ የልማት ጅምሮች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

ህገወጥ የኮንትሮባንድ ንግዱን ለመቆጣጠር የክልሉ መንግስት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከክልሉ አቅም በላይ በሆኑ አሰራሮች ላይ የፌዴራል መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮ-ሶማሌ ክልል የንግድ፣ትራንስፖርትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲረህማን አህመድ በበኩላቸው በነበረው የፖለቲካ ለውጥ ምክንያት በልማቱ ዘርፍ በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል፡፡

ህገወጥ የኮንትሮ ባንድ ንግዱን ህጋአዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ክልሉ ከጎረቤት አገሮች ጋር በብዙ ኪሎ ሜትሮች ስለሚዋሰን ችግሩን መግታት አልተቻለም ያሉት አቶ አብዲረህማን ችግሩን ለመቅፈም በድንበር አካባቢዎች የጉምሩክ ጽ/ቤቶች ተከፍተው ቁጥጥር በማድርግ  የቀረጥ ሰስርዓት ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የንግድ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ዘውዱ ከበደ በሰጡት ግብረመልስ በኢንቨስትመንት ስም ለዘመናት የታጠሩ መሬቶችን የማስመለስ ስራውን እና ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ ገብተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለውን ተነሳሽነት እና ህገ ውጥ ነጋዴዎችን ህጋአዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በጠንካራ ጎን አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በንግድ አዋጁ ላይ ማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ እንደሌለው፣ እና በክልሉ የመሰረተ ልማት ዘርጋታ ውስንነቶች እናዳሉ ያመላከቱት አቶ ዘውዱ ህገ ወጥ የኮንትሮንትሮ ባንድ ንግዱን ለመግታትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሁለንተናዊ ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡