News News

ቱሪዝም ኢትዮጵያ በአዋጅ የተሰጠውን ስራ ለመስራትና ተልዕኮውን ለመፈፀም በሚያስችለው ቁመና ላይ እንዳልሆነ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፣

ቱሪዝም ኢትዮጵያ በአዋጅ የተሰጠውን ስራ ለመስራትና ተልዕኮውን ለመፈፀም በሚያስችለው ቁመና ላይ እንዳልሆነ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፣

ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን በቱሪዝም ኢትዮጵያ የመስክ ምልከታ ካደረገ በኋላ ባዘጋጀው ሪፖርት ላይ ከተቋሙ አመራሮችና የቦርድ አባላት ጋር ተወያይቷል፡፡

ሪፖርቱን ያቀረበው ቋሚ ኮሚቴው እንዳለው ቦርዱ ከአመራሩና ከሰራተኛው ጋር ውይይት መጀመሩ እንዲሁም ቀደም ሲል በተቋሙ የነበሩ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን በጥንካሬ አንስቷል

ተቋሙ የሚመራበት ራሱን የቻለ መመሪያና አደረጃጀት የሌለው በመሆኑ ስራዎች ፍሰታቸውን ተከትለው እንደማይሰሩ እንዲሁም በአዋጅ ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር የቱሪዝም ፕሮሞሽን፣ የቱሪዝም ማርኬቲንግና የቱሪዝም ፈንድ ማቋቋምን በተመለከተ የተሰሩ ተግባራት አለመኖራቸውን ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡

ቱሪዝም ኢትዮጵያ በአዋጅ የተሰጠውን ስራ ለመስራትና ተልዕኮውን ለመፈፀም የሚያስችል ቁመና ላይ የማይገኝ መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው በተቋሙ ያለው የ6 ወር የበጀት አፈጻጸም 36 በመቶ ብቻ መሆኑና የፋይናንስ አሰራሩም ግልፅነት የጎደለው መሆኑን አንስቷል፡፡

በተለያዩ ክልሎች የተጀመሩ የመዳረሻ ልማት ስራዎች ባሉበት በመቆማቸው ከፍተኛ የተገልጋይ ቅሬታ ከመፍጠሩም ባሻገር አገራችን ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓል ያለው ቋሚ ኮሚቴው ቦርዱ ቀደም ሲል በነበሩ ሃላፊዎች የተፈፀሙ የአሰራር ብልሹነቶችን በቶሎ አጥርቶ የመፍትሔ ሃሳብ በማስቀመጥ ተቋሙን ወደ ተግባር ማስገባት ይጠበቅበታል ብሏል፡፡

በተቋሙ ባለው የመልካም አስተዳደር እጦት ሰራተኛው በተቋሙ እምነት እያጣና ተስፋ እየቆረጠ በመምጣቱ ልምድ ያላቸው ሰራተኞች ተቋሙን እየለቀቁ በመሆኑ ለሰራተኛው ምቹ የስራ ቦታ ሊፈጠርለት ይገባል ሲል ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ተቋሙ ስራውን በአግባቡ መስራት እንዲችል ከዚህ በፊት የነበሩ ህጎች ተፈትሸው ተግባራትን ለመከናወን በሚያስችል መንገድ ተስተካከልው ሊወጡ ይገባል ያለው ቋሚ ኮሚቴው ለአብነትም ተቋሙ የሚመራበትን ደንብና መመሪያ፣ የቱሪዝም ፈንድ ማቋቋምን እና መዳረሻ ልማትን አንስቷል፡፡

ለተቋሙ በቦርድነት ወይም በአመራርነት የሚመደቡ አካላት ለስራው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ቱሪዝሙን በአግባቡ በመምራት ለውጥ ለማምጣትና ሃገራችንም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችሉ መሆን አለባቸው ብሏል ቋሚ ኮሚቴው፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አክሎም ተቋሙ በአዋጅ የተቋቋመበትን አላማ ማሳካት እንዲችል ካልተደረገ የመንግስት በጀት በከፍተኛ ሁኔታ የሚባክን በመሆኑና አገራችን ለ40 ዓመታት በተለያዩ የቱሪዝም ፕሮሞሽንና የቱሪዝም ማርኬቲንግ ስራ ስትሳተፍባቸው ከነበሩ ዝግጅቶች ብታቋረጥ ከዓለም የቱሪዝም ካርታ ሊያስወጣት ስለሚችል ቦርዱና የሚመለከተው የመንግስት አካል በጋራ በመሆን ያለውን ችግር በጥልቀት በመፈተሸ   የመፍትሔ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ብሏል፡፡

የቱሪዝም ኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሰቢ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው እንዳሉት የቋሚ ኮሚቴው አስተያየት ትክክል እንደሆነና ተቋሙ አሁን ባለው ሁኔታ አለ ማለት ስለማይቻል መልሶ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለተቋሙ ዋናው ችግር የሚመደቡት አመራሮች የመንግስትን አሰራር የማውቁ እና የመምራት ብቃት የሌላቸው መሆኑ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ኃይለማሪያም ተቋሙ ካሉበት የሃብት ብክነት እንዲሁም የአደረጃጀትና አሰራር ችግሮች ወጥቶ የተጣለበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡