News News

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሁለቱ አገር የፓርላማ ተወካዮች በሂለተን ሆቴል ተወያዩ

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሁለቱ አገር የፓርላማ ተወካዮች በሂለተን ሆቴል ተወያዩ፡፡

ውይይቱ የተካሄደው መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ/ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የፈረንሳይ ፓርላማን ወክለው በመጡት የመከላከያ እና የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች መካከል ነው፡፡

በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ውይይት ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያ በምታደርገው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ፈረንሳይ ድጋፍ ለማድረግ ሙሉ ፈቃደኛ መሆኗን የፈረንሳይ ፓርላማ የወዳጅነት ቡድን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን እና በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን በዘላቂነት ለማስፈን የምታደርገውን ሁለንተናዊ ጥረት አድንቀዋል፡፡

በተመሳሳይም ኢትዮጵያና በጂቡቲ ያላቸው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የተሻለ መሆኑን ገልጸው በቻይና መንግስት የተገነባው የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር አገልግሎት አሰጣጡ ግን ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት አንጻር ሲታይ ውስንነት እንዳለበትና አገሪቱ በእዳ ጫና ውስጥ እየገባች መሆኑን አመላክተዋል፡፡      

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ ቁጥጥርና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሐመድ የሱፍ በበኩላቸው ከአውሮፓ አገሮች የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ መንግስት የወሰደው አማራጭ ቻይና በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንድታካሂድና ብድሩንም በረጅም ጊዜ የሚከፈል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የተከበሩ አቶ መሐመድ የሱፍ ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ  የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው አሁን ላይ ኢትዮጵያ በርካታ ለውጦችን እያስመዘገበች የምትገኝ ሲሆን በሶላር ኢነርጂ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመንገድ ግንባታ ዘርፎች የፈረንሳይን ድጋፍ የምትሻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፈረንሳይ መንግስት የፓርላማ ተወካዮች በተለያዩ የልማት ዘርፎች ኢትዮጵያን ለማግዝ ሙሉ ፈቃደኛ ስለመሆናቸውም ቃል ገብተዋል፡፡