News News

አርሶ አደሩ የገበያን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ምርት ባለማምረቱ ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም ተባለ

አርሶ አደሩ የገበያን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ምርት ባለማምረቱ ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም ተባለ፡፡

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት 32 መደበኛ ስብሰባው የግብርና ሚኒስቴርን የ2011 በጀት ዓመት የ8 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱ በ8 ወራት ውስጥ ሊሰሩዋቸው ካቀዱት ዋና ዋና ተግባራት በሰብል ምርት፣ በእንስሳት ሀብት ልማት፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ ወደ ተግባር ቢገባም ግብርናውን ለማዳደግ ከተቀመጠው መሰረታዊ ግብ ባጠቃላይ 4 በመቶ ብቻ መሆኑ የእቅዱን ግማሽ እንኳን ያላሳ እንደሆነ የግብርና ሚንስቴር ሚኒስትር ከቡር አቶ ኡመር ሁሴን የገለጹት፡፡

ሚ/ር መ/ቤቱ የሰብል ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አቅዶ በተንቀሳቀሰው መሰረት የአደጋ ጊዜ ሰብሎች ምርት እየጨመረ የሄደ ሲሆን የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ምርት ግን በተቃራኒው ቅናሽ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

ዕቅዱ አፈፃጸም ዝቅተኛ መሆን እንደምክንያት የተነሳው ለግብርናው ዘርፍ የሚበጀተው በጀት ከሴክተሩን ፍላጎት ጋር ያለመመጣጠን፣ የግል ባለሀብት ተሳትፎ ማነስ፣ ቴክኖሎጂን በተሟላ ሁኔታ  አለመጠቀም፣ በተገቢው በሽታን አለመከላከል እና የተሻለ ምርት ዝርያ አለመጠቀም እንደሆነ ተነስቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ትኩረት ከተሰጡ አበይት ተግባራት አንዱ የእርሻ ግብዓት የማቅረብና ስርጭቱ ማሳደግ ምርትና ምርታማነት መጨመር ወሳኝ ስራ በመሆኑ በቀጣይም የማዳበሪያ ችግርን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ የሚያችል የማዳበሪያ ፋብሪካ ከሞሮኮ መንግስት ጋር በሽርክና ለመስራት ዕቅድ ተይዞ ሲሰራ እንደቆየ የተገለጸ ቢሆንም አሁን ላይ በአንዳንድ ክልሎች የብድር አለመመለስ የግብዓት አቅርቦት ላይ ክፍተት እየፈጠረ እንደሚገኝ ም/ቤቱ አድምጧል፡፡

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ዘር አባዝተው የሚያቀርቡ የመንግስትና የግል ተቋማት ስራ በማቆማቸው የምርጥ ዘር አቅርቦት ዕጥረት እንዳጋጠመውም ነው በችግርነት የቀረበው፡፡

ሚ/ር መ/ቤቱ አርሶ አደሩ የግብርና ምርት በማሻሻል ረገድ በተለያዩ ጊዜያቶች የክህሎት ስልጠናዎች ቢሰጡም በገበያ ፍላጎት መሰረት በማድረግ የማምረቱ ሂደትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም  ዝቅተኛ መሆን ምርቱ ከፍጆታ ያላለፈ እንዲሆን አድርጓል፡፡

አገሪቱ በርካታ የእንስሳት ባለቤት ብትሆንም በተለምዶ ከማርባት ውጭ የተሻሻለ ዝርያ በመጠቀም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባት እያገኘች ካለመሆኗ ባሻገር ውጤታማ የሚያደርግ የግብይይት ስርአት ባለመኖርና የእንስሳት ማቆያና መገበያያ ቦታ በጊዜ ተገንብቶ አገልግሎት ባለመስጠቱ ቁም ከብቶቻችን ህገ ወጥ ግብይት ላይ መሆናቸው ተጠቃሚም እያደረገ እንዳልሆነ ተብራርቷል፡፡

ሚ/ር መ/ቤቱ አሁን በዓለም ቡና አምራች አገራትም ጭምር ከፍተኛ የቡና የምርት በመኖሩ ክምችቱ በዛው ልክ ከፍተኛ ስለሆነ ግብይት ሂደታችን ከጥሬ ምርት ይልቅ ተጠቃሚ የሚያደርግ እሴት በመጨመር አርሶ አደሩንንና አገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ም/ቤቱ በበኩሉ ለአርሶ አደሩ የሚቀርብ ማዳበሪያ መሬቱ የሚፈልገው አይነት ካለመሆን በተጨማሪ በጊዜ ተሰራጭቶ አለመድረሱ በምርት ላይ ክፍተት እየፈጠረ እንዳለ የጠየቀ ሲሆን ሚ/ር መ/ቤቱም የማዳበሪያ ዋጋ በገበያ ላይ በመናሩ የተከሰተ እንደሆነም መልሷል፡፡

በመጨረሻም በአገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ ኤክስፖርት የሚደረጉ የግብርና ምርቶች እንደሚታዩና ይህንንም መከላከል እንደሚገባ ጠቁሞ፤ ምርትን በአለም ገበያ በማሳወቅና የገበያ ትስስርን በመፍጠር እንዲሁም ገና ጅምር ላይ ያሉትን የአሳ ልማትና የንብ ምርት ላይ ትኩረት በማድረግ

በሌላ ዜና ምክር ቤቱ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው በመርሃ ግብር የሚከናወን መደበኛ የአየር አገልግሎት ስምምነትን ያጸደቀ ሲሆን ሁለት አዋጆችን ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በሲዊዝ ፌደራል ምክር ቤት  መካከል የተደረገው በመርሃ ግብር የሚከናወን መደበኛ የአየር ገልግሎት ስምምነት የሃገራቱን ኢኮኖሚዊ እና ማህበራዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያሳድግ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵ ፌደራላዊ ዲሞክራሲዊ ሪፐብሊክ  መንግስት እና በስዊዝ የፌደራል ምክር ቤት መካከል የተፈረመውን በመርሃ ግብር የሚከናወን መደበኛ የአየር አገልግሎት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች ግንኙነት የሚያጠናክር እና ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ የሃገሪቱን ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የቱሪዝም ፍሰት እና የዲፕሎማቲክ ግንኙነት በማጠናክር እና የአየር መንገዶችን የበረራ አድማስ ከማስፋት ረገድ ያለውን ሚና የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ አብራርተዋል፡፡ምክር ቤቱም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ከመረመረ በሗላ አዋጅ ቁጥር 1139/2011 አድርጎ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

በእለቱም የማእድን ግብይትን ለማስተዳደር እንዲሁም  የነዳጅ እና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦት እና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለማቋቋም የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ በቅደም ተከተል ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 51/2011 እና 52/2011 ብሎ በመወሰን ለዝርዝር ምርመራ ለተፈጥሮ ሃብት መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡