News News

ምክር ቤቱ ሁለት አዋጆችን አጸደቀ

 ምክር ቤቱ ሁለት  አዋጆችን አጸደቀ፡፡

ሚያዚያ 17/2011ዓ.ም ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ አመት የስራ ዘመኑ በ36ኛ መደበኛ ስብሰባው  የእንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅንና በአለም አቀፉ የልማት ማህበር መካከል ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ሽግግር እና ትስስር ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የብድር ስምምነት አዋጆችን አጽድቋል፡፡

ምከር ቤቱ የእንባ ጠባቂ ተቋምን ለማሻሻል በቀረበለት   የውሳኔ ሃሳብ በተለይም ያለመከሰስ መብትን በሚያብራራው   በአንጽ 37 ሀረግ  ዙሪያ በዝርዝር ከተወያየና በተናጠል ድምጽ ከሰጠ  በኋላ አንቀጹ ከአዋጁ እንዲወጣ በማድረግ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ   የአንድ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የስራ ስንብትን የሚመለከት ረቂቅ አዋጅ  በምክር ቤቱ  እንዲጸድቅ  ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን  ጠይቋል፡፡

ዳኛውን አስመልክቶ በቋሚ ኮሚቴው በኩል የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በምክር ቤቱ  ክርክር በማስነሳቱ ረቂቅ አዋጁ  ሳይጸድቅ ቀርቷል፡፡

የዳኛው ጉዳይ በምክር ቤቱ አባላት መካከል ሰፊ ውይይትና ክርክር ከተደረገበት በኋላ  ምከር ቤቱ በተናጠል  ድምጽ የሰጠ ሲሆን ፣ በዚህም መሰረት፣

1ኛ. የዳኞች አስተዳደር ጉባኤን ውሳኔ አንቀበለውም ያሉ የምከር ቤቱ አባላት………12

2ኛ. ዳኛው የመደመጥ መብት ተነፍጎኛል በማለታቸው የመደመጥ መብታቸው ተከብሮ ጉዳዩ  እንደገና ይታይላቸው ያሉ የምክር ቤት አባላት ……..130

3ኛ. ቋሚ ኮሚቴው ጉዳዩን በድጋሚ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያቀርብ ያሉ አባላት………134

4ኛ. ዳኛው ይሰናበቱ ያሉ አባላት …………4 እንዲሁም ተዕቅቦ 5

 ሲሆኑ፤ ጉዳዩን ቋሚ ኮሚቴው በድጋሚ አይቶ የመጨረሻ የውሳኔ ሃሳብ ይዞ እንዲቀርብ  ምክር ቤቱ  በ 134 ድምጽ  ወስኗል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስትና በአለም አቀፉ የልማት ማህበር መካከል ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ሽግግር እና ክልላዊ ትስስር ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት አዋጅ አጽድቆታል፡፡

የተገኘው ብድር 75,000,000 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር/ ሰባ አምስት ሚሊዮን  የአሜሪካን ዶላር/  ሲሆን፤ብድሩ  የሃገራችንን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ለማጠናከርና ቅድሚያ ከተሰጣቸው የኢንዱስትሪና የመሰረተ ልማት ዘርፎች  ጋር ተያይዞ ልማትን ለማፋጠን የሚረዳ አቅምን  እነደሚገነባ ተገልጿል፡፡

ብድሩ ከወለድ ነጻ ሆኖ የ6 አመታት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 አመታት ውስጥ ተከፍሎ እንደሚያልቅ ተነግሯል፡፡