News News

የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት የስራ ስምሪት መግባቢያ ሰነድ ረቂቅ አዋጅን ሲያፀድቅ ሌሎች 3 ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ መርቷል

የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት የስራ ስምሪት መግባቢያ ሰነድ ረቂቅ አዋጅን ሲያፀድቅ ሌሎች 3 ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ መርቷል፡፡

ምክር ቤቱ ጥር 29/2011 ዓ.ም ባደረገው ሶስተኛ ልዩ ስብሰባ በኢፌዴሪ መንግስትና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል የተፈረመውን የኢትዮጵያውያን የስራ ስምሪት መግባቢያ ሰነድ ለማፅደቅ የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ሳይመራ በአንደኛ ንባብ በአብላጫ ድምጽና በ26 ተቃውሞ አፅድቆታል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለስራ ከሚሰማሩባቸው የውጭ ሃገራት መካከል የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች አንዷ መሆኗን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት አብራርተው፤ መግባቢያ ሰነዱ 20 አንቀጾች ያሉት ሲሆን በኢምሬቶች ህግ መሰረት በቤት ውስጥ አገልግሎት ምድብ ውስጥ በሚገኙ ስራዎች እንዲሁም በግሉ ዘርፍ ለስራ የሚሰማሩ ሰራተኞችን ያካተተ ስምምነት እንደሆነም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

የሰራተኞች ምልመላና ስምሪት የሃገሪቱን ህግ ያከበረ እንዲሆን የማድረግ፣ የሰራተኞች መብትና ደህንነት እንዲጠበቅ እና ሰራተኞች ለጉልበት ብዝበዛ እንዳይጋለጡ የማድረግ፣ ለስራ ውሎች የህግ እውቅና እና ተፈጻሚነት የመስጠት፣ ሰራተኞች ገቢያቸውን ወደ ሃገራቸው እንዲልኩ ማስቻል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ግዴታ እንደተደነገገበት አምባሳደር መስፍን ገልጸዋል፡፡

በሌላ ዜና ምክር ቤቱ  በኢፌዲሪ መንግስትና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተፈረመውን በመርሃ ግብር የሚከናወን መደበኛ የአየር አገልግሎት ስምምነት፣ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማቀረት የትብብር መግባቢያ ሰነድ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ጥበቃ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡ 3 ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ መርቶታል፡፡