News News

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን የፌደራል መንግስት የ2011 በጀት አመት የ33.99 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን የፌደራል መንግስት የ2011 በጀት አመት የ33.99 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ፡፡

ምክር ቤቱ ከአንድ ወር የእረፍት ቆይታ በኋላ መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌደራል መንግስት የ2011 በጀት አመት ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅንና ሌሎች ሰባት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡

የመንግስት ተጠሪ ምኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት የ2011 በጀት አመት ተጨማሪ በጀት ምንጭና አስፈላጊነት ዙሪያ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት በጀቱ የተገኘው ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር እርዳታና ብድር እንደሆነና ከዚህ ውስጥ በመጠባበቂያ መልክ 33.75 ቢሊዮኑ ለመደበኛ 240,00 ቢሊዮን ብሩ ደግሞ ለካፒታል ወጪ መሸፈኛ እንዲውል ተደግፎ ቀርቧል ብለዋል፡፡

ተጨማሪ በጀቱ ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች በ2011 በጀት አመት በጀት ሲጸድቅ የነበረው የሀገር ውስጥ ብድር የበጀት ጉድለት በእቅድ ከተያዘው እንዳይበልጥ ለማድረግ፣ ክፍያቸው ላልተጠናቀቁ ካፒታል ፕሮጀክቶች፣ በቅርቡ ለሚዳሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ ወጪን ለመሸፈን፣ በሽርክና ለተቋቋመው የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት የመንግስት ድርሻ የሆነውን የመንገድና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለመሸፈን እንዲሁም በአገራችን የሚያጋጥመውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል ያገለግላል ነው ያሉት አምባሳደር መስፍን ቸርነት፡፡

ምክር ቤቱ በበኩሉ ከብድርና እርዳታ የተገኘው 33.99 ቢሊዮን ብር ለ2011 በጀት አመት ተጨማሪ በጀት ሆኖ መቅረቡ ተገቢነት ቢኖረውም አብዛኛው ለመደበኛ ወጪ እንዲውል ሲደረግ ከአገራችን የበጀት ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ መሆኑን የሚመራለት የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በትኩረት ሊመለከተው ይገባል ብሏል፡፡

ምክር ቤቱ በውሎው ሌሎች ሰባት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የመራ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፣ የንግድ ትብብርንና የስራ እድል ፈጠራን ለማጠናከር እንዲሁም በአነስተኛና መካክለኛ ከተሞች የሳኒቴሽን መሰረተ-ልማትን ለመደገፍ የሚሉ የብድር ስምምነቶች እንደሚገኙበት ለመረዳት ተችሏል፡፡