News News

ሃገሪቱ ያላትን የማዕድን ሃብት በተገቢው መንገድ እንድትጠቀም ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ሃገሪቱ ያላትን የማዕድን ሃብት በተገቢው መንገድ እንድትጠቀም ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋግ ህምራ ልዩ ዞን የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በዞኑ በሚገኙ በሳህላ እና በአበርገሌ ወረዳዎች ባደረጉት ምልከታ ሰፊ የማድን ሃብት እንዳለ ከአካባቢው ማህበረሰብ ባገኘው መረጃ ማወቅ ችሏል፡፡

በወረዳዎቹ አሉ የተባሉትን የብረት እና የወርቅ ማዕድናት አስመልክቶ ከጥናት ያለፈ በተግባር የታየ ውጤት እንደሌለ ከወረዳው አመራር በተገኘ መረጃ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ህገ ወጥ አምራቾች በህገ ወጥ መንገድ ማዕድናቱን ለገበያ እያዋሉ ነው ሲሉ የአካባቢው ማህበረሰቦች ለቋሚ ኮሚቴው ቁጭታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሃገሪቱ ያላትን የማድን ሃብት ከማስጠበቅ እና ህገ ወጥ የማዕድን አምራቾችን ከመከላከል  በተለይም ወጣቱን የሃብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማስቻል እና የስራ እድል ከመፍጠር፣   ባህላዊ የማዕድን አምራቾችን በማደራጀት ወጣቱ ወደ ስራ እንዲገባ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ካማስጨበጥ አኳያ ማዕድን ሚንስቴር ክፍተቶች እንዳሉበት ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይም ቋሚ ኮሚቴው በወልድያ እና በኮምቦልቻ ያለውን የመብራት ሃይል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተመልክቷል፡፡ የፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ 18 ወራት ቢሆንም አሁን 13ኛ ወራት ላይ መሆኑንና የወልድያው ሲቪል ፓርቱ 65% የኮምቦልቻው 60% ሲሆን የቀረው ኤሌክትሪካል ፓርቱ በበጀት እጥረት ምክንያት ያልተጀመረ በመሆኑ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት ሆኖብናል ሲሉ የፕሮጀክቱ የስራ ሃላፊዎች ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የኮምቦልቻ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያን አስመልክቶ ካሳ ተከፍሏቸው ቦታውን ያልለቀቁ አርሶ አደሮች እንዳሉ እና ፕሮጀክቱ ስራውን በተገቢው መንገድ እንዳይሰራ እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቅሰው የከተማ አስተዳደሩን እገዛ የሚሹ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አንስተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም በፕሮጀክቱ የስራ ሃላፊዎች የተነሱትን ጥያቄዎች ለኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ያነሱ ሲሆን በምላሹም የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከድር እንድሪስ እንዳሉት የካሳ ክፍያን አስመልክቶ አርሶ አደሩን በማወያየት ሰፊ ስራ እንደሰሩ ጠቅሰው ያሉትን በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍ የፕሮጀክቱ ስራ በተባለለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ፕሮጀክቱ በተባለበት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ለአርሶ አደሩ ተለዋጭ ቦታ በመስጠትና ቦታውን እንዲለቁ በማድረግ ረገድ ከተማ አስተዳደሩ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚጠብቀው ጠቁሞ ከፕሮጀክቱ የስራ ሃላፊዎች እና ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡