News News

በየጊዜው የሚጀመሩ የመንግስት ልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መጠናቀቅ እንዳለባቸው ተገለጸ

በየጊዜው የሚጀመሩ የመንግስት ልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መጠናቀቅ እንዳለባቸው ተገለጸ

ይህ የተባለው የፌዴራል መንግስት የ2012 ረቂቅ በጀት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፋዊ የህዝብ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው፡፡

ለአገሪቱ የሚመደበው በጀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም በሚጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የአፈጻጸም መጓተት እንደሚስተዋል የተገለጸ ሲሆን በሌላ በኩል የዋጋ ግሽበቱ እያሻቀበ መምጣቱ በውይይቱ ተነስቷል፡፡

በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በኢንዱስትሪ ርኮች እና በመስኖ ፕረሮክቶች ዙሪያ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ ከውይይቱ ተሳታፊዎች  ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በመሰረተ ልማት ዝርጋታ በተለይም በመንገድ ግንባታ እና በኤሌክትሪክ ዝርጋታ ዙሪያ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉ እና መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡

በተመሳሳይም በሚጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ መጓተት የሚታየው ከእቅድ ዝግጅት፣ ከማስፈጸም አቅም ማነስ እና ከቁጥጥር መላላት የመነጨ እንደሆነ የገልጹት ዶክተር እዮብ ችግሮችን በየፈርጁ ለመቅረፍ በ2012 በጀት ዓመት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አመታት ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁትን የመስኖ ፕሮጀክቶች በ2012 በጀት ዓመት ለማስፈጸም፣ እንደዲሁም ተጨማሪ አዳዲስ 10 የመስኖ ኘሮክቶችን ለመገንባት መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ሚኒስትር ድኤታው ዶክተር እዮብ አስረድተዋል፡፡

ጂኤጂን አስመልክቶ ለተነሳው ጥያቄም ዶክተር እዮብ ምላሽ ሲሰጡ የደረጃና የደመወዝ ማስተካከያ ለማድግ ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው አፈጻጸሙ ግን ሂደታዊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

በሌላ በኩል ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ማስፈጸሚያ ሚበጀተው ገንዘብ በቀመር ሊሆን አይገባም፣ ለአገሪቱ የሚያስገኙት ጥቅምና ፋይዳ ተሳቢ ተደርጎ መሆን አለበት የሚል በውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይም በአገሪቱ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ በመምጣቱ በህዝቡ ዘንድ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች  ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተካበሩ ወ/ሮ ለምለም ሀደጉ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ ክፍተቶች እንደነበሩ ገልጸው በ2012 በጀት ዓመት ዳግም የኢኮኖሚ መዋዠቅ እንዳይከሰት ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት እና ዜጎችም ከሚያገኙት ገቢ ለአገራቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርንት እንዲችሉ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡