News News

ምክር ቤቱ የትብብር ስምምነቶችን አጸደቀ

ምክር ቤቱ የትብብር ስምምነቶችን አጸደቀ፡፡

አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ባደረገው 18ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡

በተለይም ከሞሮኮ ንጉሳዊ መንግስት ጋር በኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ጥበቃ ዘርፍ እና በግብርና ዘርፍ ለመተባበር የተፈረሙ ስምምነቶች የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ በማሳደግ፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማጎልበት እና በበረሃማ ቦታዎች ሞሮኮ ያላትን የማልማት ቴክኖሎጂና ዕውቀት በማሸጋገር እንደሚጠቅሙ ምክር ቤቱ በማመን ስምምነቶቹ በቅደም ተከተል አዋጅ ቁጥር 1106/2011 እና አዋጅ ቁጥር 1107/2011 ሆነው እንዲፀድቁ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

እንደዚሁም ከሩዋንዳ ሪፐብሊክ መንግስት ጋር በኮሙኒኬሽንና በሚዲያ ዘርፍ እና በግብርና ዘርፍ ለመተባበር የተፈረሙ ስምምነቶች አገሪቷ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆኗ በመዲናዋ የሚደረጉ የውይይት መድረኮችን በመመዝገብ እና መረጃን ለተለያዩ አገራት በማዳረስ የአገሪቱን ገፅታ ለመገንባት እና ሩዋንዳ በግብርና ዘርፍ ራሷን በመመገብ በግብርና ኢንዱስትሪ የላቀ ዕድገት ያሳየች በመሆኗ ከሷ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ እንደሚጠቅሙ ምክር ቤቱ በማመን ስምምነቶቹ በቅደም ተከተል አዋጅ ቁጥር 1108/2011 እና አዋጅ ቁጥር 1109/2011 ሆነው እንዲፀድቁ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል የተደረጉ አራት ስምምነቶችን መርምሮ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት በዋናነት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲሆን በተባባሪነት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ናቸው፡፡