News News

የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን መብትና ነጻነት አላግባብ የማይገድብና መንግስት ህጉን የፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያና መጠቀሚያ የማያደርግ መሆን አለበት ተባለ

የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን መብትና ነጻነት አላግባብ የማይገድብና መንግስት ህጉን የፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያና መጠቀሚያ የማያደርግ መሆን አለበት ተባለ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ አባላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱም የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የጠቅላይ አቃቤ ህግና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የሽብር ድርጊት በዓለም ሰላም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ከሆኑ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን በየጊዜው በተለያዩ አገራት ላይ እየተፈጸመ የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ በመሆኑ አገራት በጋራና በተናጠል ለመቆጣጠር ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውና የተባበሩት መንግስታትም በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የውሳኔ ሃሳቦችን ማስተላለፉ ተብራርቷል፡፡

ኢትዮጵያም በውስጥም ሆነ በውጭ ስጋት ያለባትና የድርጊቱ ሰለባ በመሆኗ እ.ኤ.አ መስከረም 2001 ዓ.ም አባል አገራት ላይ ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚረዱ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ግዴታ የሚጥል የውሳኔ ሃሳብ በመቀበል ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንዳለችና በተለይ እንደ ዓለም አቀፍም ሆነ እንደ አፍሪካ ስራ ላይ የዋለውን ሽብርተኛን በገንዘብ መርዳት ለመቆጣጠር የወጣውን ስምምነት የተፈራረመችውን ስራ ላይ ለማዋል እንደሆነም ነው በማብራሪያው የተቀመጠው፡፡

ከቋሚ ኮሚቴዎችና ከም/ቤት አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ምላሽም ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከትርጉም፣ ከይዘት እና አዋጁ ከዚህ በፊት ተግባራዊ እየተደረገ ካለው ጸረ-ሽብር አዋጅ በዓላማ ይዘቱ በምን እንደሚለይ የጠየቀ ሲሆን የነበረው አዋጅ ህብረተሰቡን ያላሳተፈ፣ የዜጎችን መብትና ነጻነት አላግባብ የሚገድብ እንዲሁም መንግስት ህጉን የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካት በተለይም የሚቃወሙትን አካላት ለማጥቂያ መሳሪያነት መጠቀሚያ ነው በሚል ሲነሳ የነበረውን ቅሬታና ትችት ለውጡን ተከትሎ የዜጎችን መብትን አላግባብ የሚገድቡ ህጎችን ቃል በተገባው መሰረት ለማሻሻል እንደሆነም የጠቅላይ አቃቤ ህግ አስረጂዎች አብራርተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በትርጉም ክፍል በተቀመጡት ላይ ማደም፣ መዛት፣ መሰናዳት እና አድማ የሚሉ አገላለጾች ከመደበኛ ህጎች ጋር ያላቸው አሻሚነትን ለመቀነስም ጠይቆ አዋጁ በመሰረታዊነት ሽብርን ለመቆጣጠር ሚያስችሉትን ትኩረት በማድረግና ህጎችም እርስ በርስ እንዳይጣረሱ ለማድረግ እንደተሞከረም ነው ምላሽ የተሰጠው፡፡           

ቋሚ ኮሚቴው አዋጁ ዜጎች መብታቸውን እንዳይጠይቁ፣ ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳያራምዱ እንዲሁም ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማጥበብ የወጣ አዋጅ እንዳይሆን የመሰየም ስልጣን ለምክር ቤቱ የተሰጠው መሆኑ ተገልቷል፡፡

አዋጁ ከቀላል እስከ ከባድ የያዘ ሲሆን የሽብር ወንጀል ለመፈጸም የማቀድ ተግባር የፈጸመ ከ3-7 ዓመት ጽኑ እስራት ሲያስቀጣ አንቀጽ 3(2) ላይ ወንጀሉን ፈጽሞ የተገኘ ደግሞ ከ18- ዓመት እስከ እንድሜ ልክን አልፎም እስከ ሞት ሲደነግግ በተለይ ከሽብር ድርጊት ክብደት አንጻር ከጅምር ሃሳብ አንስቶ እስከ አፈጻጸም የሚሸፍን ከፍተኛ ጉዳትም የሚያደርስ ተግባር እደሆነም ነው፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አዋጁ በአንቀጽ 8 ላይ በተቀመጠው ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር ለጠየቀው ጥያቄ አሁን እንደ አገር በሚታየው ማህበራዊ ሚዲያ ወይም ፌስቡክ አሉታዊ የሀሰት መልዕክት ስርጭት ሁኔታ በተመለከተ የሚያተኩርና በተለይ መረጃው በሽብር ድርጊት የሚገለጽ ከሆነ ከሀሰት ማስፈራያ ጋር የሚያያይዝም እንደሆነ ነው በማብራያው የተገለፀው፡፡