News News

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለኦዲት ግኝቶች ፈጥኖ ምላሽ መስጠት አለበት ሲል የመንግስት ወጪና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለኦዲት ግኝቶች  ፈጥኖ ምላሽ መስጠት አለበት ሲል  የመንግስት ወጪና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ.ም በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2009 በጀት አመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርትን አደምጦ  ተወያይቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የተቋሙን የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት የገመገመው የፌደራል ዋና ኢዲተር መ/ቤት ባካሄደው  ኦዲት ግኝት መሰረት ነው፡፡ የሂሳብ ምዝገባዎችን ተከታትሎ አለመመዝገብ፣ ከሌሎች የሚሰበሰቡና ለሌሎች የሚፈጸሙ ክፍያዎችን በትክከለኛ ተቀጽላ ሌጀር የማይመዘገብ መሆኑ፣ሂሳብ ተዘግቶ ወደሚቀጥለው በጀት አመት የሚተላለፉ ሂሳቦች በትክከለኛ የሂሳብ መደብና ሚዛን የማይመዘገቡ መሆኑን የኦዲት ግኝቱ እንደሚያሳይ  ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል፡፡

ግብር እንደሚከፈልበት እየታወቀ የቤት አበል የሚከፈላቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ከደሞዛቸው ጋር ተደመሮ ሊቀነስ ሲገባ  ያልተቀነሰ የገቢ ድምር ብር 234,077.27 እና ሳይታረም ቆይቶ በክትትል ኦዲት የተገኘ ያልተቀነሰ ግብር ብር 4,667,182.10 መገኘቱን  ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ያለግልጽ  ጨረታ  የብር 10,000,000.00 የግንባታ ግዢ ለአንድ ድርጅት መስጠቱን  እና ሌሎች ከመንግስት የፋይናንስ አሰራር ውጪ የተፈፀሙ ክፍያዎችን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ከቋሚ ኮሚቴው  በኩል ተነስተው፤የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ  መአዛ አሸናፊ  እና ከሌሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር ሆነው ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡

የመንግስትን ፋይናንስ አሰራር ህጎችን ማክበርና ማስከበር የተቋሙ ግዴታ   መሆኑን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ  መአዛ አሸናፊ ገልፀው፤  ክፍተቶችን ለመሙላት የተደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አስገንዝበዋል፡፡ የሂሳብ አመዘጋገብን በሚመለከት የሂሳብ ክፍተት የታየባቸው መለየታቸውንና የተስተካከሉ እንዳሉም ነው የጠቆሙት፤የዳኞች የቤት አበል ግብር በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱ እንዳሉት ደሞዛቸው አነስተኛ በመሆኑ ምክንያትና ከነበረው ችግር አንጻር የዳኞች አስተዳደር ተወያይቶ ለጊዜው እንዲቀር ቢደረግም አሁን መከፈል መጀመሩ ታውቋል፡፡የግንባታ ግዢን በሚመለከት  በወቅቱ የነበረውን ብዙ እሮሮና ችግር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በታለመ የተደረገ እንጂ ያለ አግባብ የባከነ ገንዘብ እንደሌለ እና እርምጃ የተወሰደባቸውና የተስተካከሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ፕሬዚዳንት ወ/ሮ  መአዛ አሸናፊ    አብራርተዋል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስራ ቤት  ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው ተቋሙ የሂሳብ ምዝገባ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበት ጠቁመው፤ የገቢ ግብርን በሚመለከትም  በሕጉ መሰረት መመለስ እንዳለበት  አንስተዋል፤ የተቋሙ የግንባታ ግዢ   አካሄዱ ትክክል እንዳልሆነና ህጉን ተከትሎ መሄድ እንዳለበት ጠቁመው፤ የተስተካከለና የተወሰደ እርምጃ ካለ ተቋሙ  ቢያሳውቅ ጥሩ  መሆኑንና ድጋፍ የሚፈልጉም ከሆነ አሰፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዘግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ተቋሙ ደንብና መመሪያን ተከትሎ መስራት እንዳለበት፣ከግዢ ጋር ተያይዞ ህጎቹ በአግባቡ ሊተረጎሙ እንደሚገባ፣የኦዲት ግኝቶችን የታረመና ያልታረመ ለይቶ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ እና በዋና ኦዲተር የተሰጠውን አስተያየት ተቀብሎ ማስተካከል ለግኝቶቹም ፈጣን  እርምጃ መውሰድ  እንደሚያስፈልግ  አንስቷል፡፡