News News

ሴቶች በግጭት አፈታት እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ያላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ሴቶች በግጭት አፈታት እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ያላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለፀው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በሰላም ሚኒስቴር በተዘጋጀው የሴት አፈ ጉባኤዎች የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ የውይይት መድረኩ ‘’ሴት አፈ ጉባኤዎች ለሰላም’’ በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን  የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ መሃመድ፣ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል፣ከክልል፣ከከተማ አስተዳደር እና ከወረዳ የመጡ ሴት አፈ ጉባኤዎች ተሳትፈዋል፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባአኤ ወ/ሮ ኬሪያ መሃመድ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ በሃገራችን እያጋጠመን ያለው የሰላም እጦት ማህበራዊ አንድነታችንን እያናጋው በመሆኑ በብዝሃነት የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ አንድነትን በማጎልበትና የተጀመረውን የመለወጥ ፍላጎት እውን ለማድረግ የሴቶችን እምቅ አቅም በመጠቀም ሴት አመራሮች ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

አያይዘውም የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊ በመሆኑ ተቋማዊ አሰራርን በማጎልበት እንዲሁም ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎቻችንን በማጠናከር በዕርቀ ሰላም ዙሪያ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በእለቱም ሴቶች በግጭት አፈታትና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ያላቸውን ሚና አስመልክቶ ወ/ሮ ኡባህ መሃመድ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም በግጭት ሂደት ሴቶች ለሰላም ያላቸው አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን ጠቅሰው የሴቶችን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ማሳደግ የምንችለው ሰላም ሲኖር በመሆኑና እኛ ሴቶች በሃገራችን ብልጭ ድርግም በሚለው የሰላም ችግር ተጋላጭ እንደመሆናችን በግጭት አፈታት ሂደት ውስጥ ሴቶች የራሳቸው የሆነ የተለያየ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የምክር ቤቶቻችን ሚና ሰፊ በመሆኑ የጋራ እሴቶቻችንን በማጠናከርና ህገ መንግስታችንን በማስከበር ጥሰትን የማይቀበል ዜጋ ከማፍራት ረገድ ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው ሰላምን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ የህዝብ ሰላም ለህዝቦች ተጠቃሚነት ወሳኝ በመሆኑ አቅም ያላቸው ህብረተሰባዊ መሳሪያዎቻችንን ተጠቅመን እሴቶቻችንን ማእከል ያደረገ ሰላም መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡እክለውም እኛ ሴቶች ከሰራን የሰላም መገኛ መሆን ስለምንችል ብልህ ሆነን በሃገራችን ያጋጠመንን የሰላም ችግር ወደ መልካም ከቀየርን ማሳካት የምንፈልገውን ሃገራዊ ድል ማሳካት እንችላለን ብለዋል፡፡