Participate Participate

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ አጭር ማብራሪያ

Threads [ Previous | Next ]
መግቢያ

በዘመናዊ የዲሞክራሲ ስርዓትና አስተሳሰብ ምርጫና የፖለቲካ ፖርቲዎች ሊተካ የማይችል ፋይዳ አላቸው፡፡ ከዚህ የተነሳ የፖለቲካ ፖርቲዎችንና ሌሎች የፖለቲካ ማህበራትን ወይም ድርጅቶችን የማስተዳደር (Regulate) እንዲሁም የምርጫን የማስፈፀም ስራ የሚሠሩ ተቋማት በዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ጠንካራ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋማት(Electoral management Bodies) በሌሉበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓትንም ሆነ ትርጉም ያለው ምርጫን ማካሄድ አዳጋች ነው፡፡የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት ከፀደቀበት ጀምሮ በተካሄዱት ምርጫዎች ላይ እጅግ አወዛጋቢ ከሆኑና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ተግዳሮት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል በሕገ መንግስቱ የተቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቃትና ገለልተኝነት ነው፡፡ ቦርዱ በፖለቲካ ፖርቲዎችም ሆነ በህዝቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ዝቅተኛ መሆን፣ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት የማይመች አደረጃጀትና ሌሎች መሰል ችግሮች ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ትልቅ እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል፡፡ መንግስት ተግባራዊ እያደረገ ባለው የዲሞክራሲና የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቁርጠኛ አቋም የተያዘ ሲሆን ይህንን አቋም በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድንና ተያያዥ ሕጐችን በመፈተሽ፣ ችግሮችን በመለየት አግባብነት ያላቸውን የመፍትሄ ዕርምጃዎች መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ይህንንም ከግምት በማስገባት በጥናት ላይ በመመርኮዝ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን ለመወጣት ያሉበትን ውስንነቶች እንዲሁም የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመለየት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር አስፈላጊውን ምክክር በማድረግ ይህ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ጠንካራ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የሆነ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም ለማደራጀት ምቹ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡

የረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ሂደት 

የረቂቅ አዋጁን በማዘጋጀት ሂደት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያቋቋመው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔና ጉባኤው የዲሞክራሲ ተቋማትን በተመለከተ ኃላፊነት የሰጠው የሥራ ቡድን ኃላፊነቱን ወስደው ሰፊ ስራዎችን ሠርተዋል፡፡በቅድሚያ የሥራ ቡድኑ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የተመለከቱ የሕግ፣ የመዋቅርና የአሠራር ችግሮችን በጥናት የለየ ሲሆን የጥናት ግኝቶቹን ለአማካሪ ጉባዔውና ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ግብዓት አሰባስበዋል፡፡ በመቀጠልም የሥራ ቡድኑ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር በመተባበር በጥናቱ ተመርኩዞ ከውይይት መድረኮች የተገኘውን ግብዓት ከግንዛቤ በማስገባት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በድጋሚ የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ አዘጋጀቷል፡፡ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ለመገምገምና ለማዳበር ከባለድርሻ አካላት፣ ከአማካሪ ጉባኤው እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ሰፊ ልምድና እውቀት ካላቸው የውጭ ሃገር ባለሞያዎች ጋር ምከከር አድርጓል፡፡በዚህ ሂደት በተለይም ከምርጫ ቦርድ አዲስ አመራርና ከፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር በቅርበት በመመካከር ግብዓት ለማሰባሰብ ጥረት ተደርጓል፡፡

በጥናትና በውይይት የተለዩ ቁልፍ ግኝቶች

የሥራ  ቡድኑ ባካሄደው ጥናትና የውይይት መድረክ የተገኙት ቁልፍ ግኝቶች የሚከተሉት ናቸው፡-

 • ነፃነትና ገለልተኝነት

የሥራ ቡድኑ ጥናት እንደሚያሳየው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነፃነትና ገለልተኝነት ላይ ብዙ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የቦርዱ አባላት አሰያየም፣ የሥራ ሁኔታና የቦርዱ የሕግ ማዕቀፍ የቦርዱን ነፃነትና ገለልተኝነት በበቂ ሁኔታ አላስጠበቀም የሚል ቅሬታ በተለያዩ የባለድርሻ አካላት ዘንድ ይንፀባረቃል፡፡  ይህንን አይነት አመለካከት በህብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት ዘንድ በስፋት የሚንፀባረቅ መሆኑ በራሱ የቦርዱን አቅምና ውጤታማነት በእጅጉ እንደሚገድበው እሙን ነው  ፡፡፡፡ በተለይም የቦርዱ አባላት የሚመለመሉበት ግልፅ አሰራር ባለመኖሩ፣ የቦርዱ አባላት የአሿሿም ስርዓት በበቂ ሁኔታ የባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ አለመሆኑ፣ የቦርዱ አባላት በስራቸው ላይ ሳሉ አግባብ ካልሆነ ተፅዕኖና ግፊት የሚጠበቁበት ሁኔታ ስላልተመቻቸ የቦርዱ ነፃነትና ገለልተኛነት አጠያያቂ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት ሪፎርም ኪደረግባቸው ዘርፎች መካከልም አንዱ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

 • አቅምና መዋቅር

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት አሁን ባለው አደረጃጀትና መዋቅር ቦርዱን የሚያገለግሉት በትርፍ ጊዜ የቦርድ አባልነት ነው፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ውጪ ያሉት ሰባት የቦርድ አባላት በቦርዱ ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በቂ ጊዜ ሰጥተው በቦርዱ ስራ የማይሳተፉ በመሆኑ ቦርዱ ላይ የአቅም ውሱንነት አስከትሏል፡፡የቦርዱ አባላት የቦርዱን ስራ ጠንቅቀው አውቀውና ተረድተው፣ በቂ አመራር ለመስጠትና ክትትል ለማድረግ አይችሉም፡፡ ከዚህም የተነሳ የቦርዱን ስራ የሚሠራው የቦርዱ ጽህፈት ቤት ነው፡፡ በዚህ ሂደት በቦርዱ አባላትና በጽህፈት ቤቱ መካከል ክፍተት የሚፈጥርና አልፎም የአለመግባባቶች ምክንያት ሆኗል፡፡ የባለድርሻ አካላትና የፖለቲካ ድርጅቶችም ከቦርዱ ጋር ባላቸው ጉዳይ የቦርዱን አባላት ማግኘት እንዳይችሉ፣ በቦርዱ ላይ ያላቸው አመኔታም እንዲቀንስ አንድ ምክንያት ሆኗል፡፡ከዚህም በመነሳት የሚከተሉት የማሻሻያ እርምጃዎች አስፈላጊ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

 • የቦርዱን አባላት አሰያየም ግልፅና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚያረጋግጥ እንዲሆን ማድረግ፡፡

 • ለቦርዱ አባልነት የሚሰየሙ ሰዎች የቦርዱን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ሙያዊ ብቃትና አቅም ያላቸው፣ እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት፡፡

 • የቦርዱን ገለልተኝነትና ነፃነት ለማረጋገጥ የሚረዳ፣ቦርዱን ከየትኛውም አካል ተፅዕኖ ለመጠበቅ የሚያግዝ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ፣

 • የቦርዱ አባላት በሙሉ ጊዜያቸውን በንቃት በቦርዱ ስራ ላይ እንዲሳተፉ፣ ቦርዱ በስም ቦርድ ቢሆንም በተግባርና በአወቃቀሩ በተቻለ መጠን የኮሚሽን አይነት ባህሪ እንዲኖረው የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት፣

 • የቦርዱ አባላት የሥራ ሁኔታና የሥራ ዘመን የቦርዱ አባላትን ነፃነትና አቅም የሚያጠነክር እንዲሆን ማድረግ፣

 • ቦርዱ ሥራ ማስፈፀሚያ በጀቱን የሚያገኝበት መንገድ ነፃነቱን የሚያስጠብቅና በተገቢው ሁኔታ ኃላፊነቱን ለመወጣት ምቹ እንዲሆን ማድረግ፣

 • ቦርዱ እንዳስፈላጊነቱና በተቀናጀ መንገድ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች በቂ ምላሽ መስጠት የሚያስችለው አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነ በተደረገው ጥናትና ምክክር ተመላክቷል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ተግባራዊ የሚደረጉ ለውጦችና የረቂቁ አንኳር ይዘት


በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የተቋቋመበት አዋጅ “የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 53/2/1999” ነው፡፡ ይህ አዋጁ የምርጫ ቦርድን ከማቋቋሙ በተጨማሪ በሃገሪቱ የሚካሄዱ የተለያዩ ምርጫዎችን የሚገዛ የሕግ ማዕቀፍ ይደነግጋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ አዋጅ 532ን ሙሉ በሙሉ የሚተካ ሣይሆን የምርጫ ቦርድን የሚመለከተውን ክፍል ብቻ የሚተካ ነው፡፡ ይህ የደተረገው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡አንደኛ ለቀጣዩ ምርጫ የቀረው ጊዜ አጭር ከመሆኑ የተነሳ፣ ለምርጫው ዝግጅት ለማድረግና ቦርዱ ተገቢውን ተቋማዊ ማሻሻያ ለማድረግ በተቻለ ፍጥነት ቦርዱን መልሶ ማዋቀር አስፈላጊ በመሆኑ፤ አዋጅ ቁጥር 532/1999ን ሙሉ በሙሉ ለማሻሻል ረዘም ያለ ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ በቅድሚያ ቦርዱን እንደገና የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጁ አዘጋጅቶ በቀጣይነት ደግሞ ቀሪውን የአዋጅ ቁጥር 532/1999 ክፍሎች ወጥ በሆነ መልኩ የሚያሻሽል አዋጅ ማዘጋጀት ተመራጭ ሆኗል፡፡ሁለተኛ በሌሎችም ሃገሮች/ለምሣሌ በኬንያና በደቡብ አፍሪካ/ የምርጫ ሂደትን የሚገዛውን ሕግን የምርጫ አስፈፃሚውን የሚያቋቁመውን ሕግ ሁለት የተለያዩ ሕጐች ማድረግ የተለመደ መሆኑ፤ ይህም አሠራር የምርጫ ሕጉን ወይም የምርጫ አስፈፃሚውን ማቋቋሚያ አዋጅ ማስተካከል በሚያስፈልግ ጊዜ በቀላሉ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ስለሚያመች ይህ አካሄድ ተመርጧል፡፡ረቂቅ የምርጫ ቦርድ መቋቋሚያ አዋጁ ተግባራዊ የሚያደረጋቸው ለውጦችና በስራ ላይ ካለው አዋጅ የሚለይባቸው መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፡-

 1. ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ማለትም የተቋሙና የተቋሙ አካል የሆነው የተቋሙ ቦርድ መካከል ለመለየት የሚያስቸግርና የሚያምታታ አገላለፅ ነበር፡፡ ይህንን ውዥንብርና ከዚህም የሚከተለውን የሥልጣንና የኃላፊነት መምታታት ለማስወገድ በቦርዱ አቋም ውስጥ “የስራ አመራር ቦርድ” በማቋቋም የተቋሙ መዋቅር ላይ የተሻለ ግልፅነት እንዲኖር ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ቦርድ የሚለው ተቋሙን የሚገልፅ ሲሆን የስራ አመራር ቦርድ የሚለው የሰዎቹን ስብስብ  እንዲገልፅ ተደርጎ ተረቋል፡፡

 2. የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ቁጥር ከዘጠኝ ወደ አምስት ተቀንሶ፣ የስራ አመራር ቦርዱ አባላት ሁሉ በሙሉ ጊዜ ቦርዱ ውስጥ የሚያገለግሉ ተሿሚዎች እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ከዘጠኝ ወደ አምስት የወረደበት ምክንያት ቋሚ ሆነው ከሰሩ አምስቱ ውጤታማ ስራ የሚሰሩ መሆኑ ስለታሰበ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ስራዎችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወንና  የመንግስትንም ወጪ ለመቀነስ ታስቦ ነው፡፡ ሌላው ዘጠኝ የቦርድ አባላት በቋሚነት የሚሰሩት ስራ ይኖራል ወይ የሚለውም ከግምት ገብቷል፡፡ ቋሚ የተደረጉት  ቦርዱ በንቃት በስራው የሚሳተፉ አመራሮች እንዲኖሩት ለማስቻል ነው፡፡

የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የቦርዱን ዓላማ ፈፃማ የስራ ሂደቶች በኃላፊነት በምመራት ቦርዱ የኮሚሽን አይነት ተቋማዊ ቅርፅና ባህሪ እንዲኖረው ማድረግ በባለድርሻ አካላት ዘንድ ያለ ፍላጐትና የቦርዱን አቅምና ጥንካሬ ለመጨመር የሚያግዝ አሠራር በመሆኑ ይህ በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡ የሥራ አመራር ቦርዱ አባላት በሙሉ ጊዜያቸውን በቦርዱ ስራ የሚያሳልፉ ተሿሚዎች ሲሆኑ ይህ የሚያስከትለውን ወጪ ታሣቢ በማድረግ፣ ከላይ እንደገለፅነው የቦርዱ ኃላፊነት የሚጠይቀውን የአመራር ብዛትም ከግምት በማስገባት የተሿሚዎችን ቁጥር ከ9 ወደ አምስት ተቀንሰዋል፡፡

 1. የስራ አመራር ቦርዱ አባላት አሰያየም ግልፅ የባለድርሻዎችን ተሳትፎ የሚያሳድግና በምርጫ አስፈፃሚው አካል ላይ ህዝቡም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች እምነት እንዲያሳድሩ ለማድረግ የሚረዳ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ይህ ስርዓት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ አባልነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሾሙትን ዕጩዎች በመመልመል ሂደት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ለማድረግ የታሰበ ነው፡፡ በመሆኑም የቦርድ አባል የሚሆኑ እጮዎችን የሚመለምል  የጠቅላይ ፍርድ ቤት ተወካይ ከኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ፣ከኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌደሬሽን፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ም/ቤት፣ከኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን እና ከሲቪል ማህበራትና ካገር ሽማግሌዎች የሚመረጡ 3 ሰዎችን ያካተተ ኮሚቴ እንደሚቋቋም  በአዋጁ ተመልክቷል፡፡ ይህም የተደረገው በማህበረሰቡ ዘንድ ተአማኒነት ያላቸውን የቦርድ አባላት ለመምረጥ እንዲቻል ነው፡፡

 2. ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውስጣዊ መዋቅር ጋር በተገናኘ፣ በተለይም በቦርዱ ፅህፈት ቤትና በቦርዱ የስራ አመራር አባላት ዘንድ ያለው የሥራ ክፍፍልና ኃላፊነት ይበልጥ ግልፅ በማድረግ የቦርዱ ስራ እንዲቀላጠፍ ለማስቻል ጥረት ተደርጓል፡፡

 3. አሁን በስራ ላይ ባለው የምርጫ ህግ መሠረት የቦርዱ አባላት የሚያገለግሉት ለአምስት ዓመት ሲሆን ሁሉም የቦርድ አባላት የሚሾሙትና የሥራ ጊዜያቸው የሚያበቃው በአንድ ጊዜ ነው፡፡ ይህ አሠራር ሁለት ችግሮች ያስከትላል፡፡ በመጀመሪያ በየአምስት ዓመቱ የቦርድ አባላት በሙሉ ስለሚለወጡ ቦርዱ ተቋማዊ ትውስታ (institutional Memory) በበቂ ሁኔታ አይኖረውም፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ልምድ ያካበቱ የቦርድ አባላት በሙሉ በአንድ ጊዜ ከኃላፊነት ስለሚሰናበቱ ያገኙትን ልምድ ለአዳዲስ አባላት አብሮ በመስራት ሂደት ሊያስተላልፉ አይችሉም፡፡ ከዚህም በላይ የቦርዱ አባላት የሥራ ዘመን በ5 ዓመት የተገደበ መሆኑ በቂ ልምድ ለማግኘት የሚያስችል፣ ከምርጫ ዑደት ጋር የተጣመረ መሆኑ ደግሞ የቦርዱ ገለልተኛነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሣድር የሚችል ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ በረቂቅ አዋጁ የሥራ አመራር ቦርዱን አባላት የሥራ ዘመን እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የስራ አመራር ቦርዱ አባላት አሿሿም በተለያየ ጊዜ እንዲሆን (Staggered appointment) እንዲሆን ተደርጓል፡፡

 • አመራር ቦርዱን አባላት ነፃነት ለማጠናከርም የቦርድ አባላት በድጋሚ ለመሾም የማይችሉ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

 1. የቦርዱን አባላት ነፃነት ለማስጠበቅ በረቂቅ አዋጁ የተደነገገው የቦርድ አባላት ከኃላፊነታቸው ሊነሱ የሚችሉባቸውን ምክንያቶችና ስርዓት ነው፡፡ እነዚህ ምክንያቶችና የተዘረጋው ስርዓት በቂ እና አሳማኝ ምክንያት ከሌለ በስተቀር የቦርድ አባላትን ከኃላፊነታቸው ማውጣትን አዳጋች ስለሚያደርገው የቦርድ አባላትን ነፃነት ለማስጠበቅ አስተዋፆኦ ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም የቦርዱን አባላት ለመሾምም ሆነ ከኃላፊነታቸው ለማንሳት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2/3 ድምፅ ማስፈለጉ አባላቱ ሰፊ ተቀባይነት ከሌላቸው እንደማይሾሙ፣በጣም አሳማኝ የሆነ ምክንያት በሌለበት ደግሞ ከኃላፊነታቸው እንደማይነሱ ጥበቃ በመስጠት ነፃነታቸውንና ገለልተኝነታቸውን ያጠናክራል፡፡

0 (0 Votes)

Quick Reply