Participate Participate

የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ

Threads [ Previous | Next ]

የአዋጁ አስፈላጊነት

ተመድ( የፀጥታው ምክር ቤት) እ.ኤ.አ በ2004 ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን በተመለከተ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ይህም በ ተመድ ውሳኔ ቁጥር 1540/2004 ተመዝግቦ የሚገኘው ውሳኔ ነው፡፡ በዚህ ውሳኔ ጅምላ አውዳሚ መሣሪያዎች የሆኑት የአስኳል ጉልበት (nuclear)፣ የንጥረ-ነገር (chemical)፣ የረቂቅ-ተውሳክ (biological) እና እነሱን ተሸካሚ የሆኑ መሣሪያዎች የዓለም ሰላምና ጸጥታ ስጋት መሆናቸውን፤ ከእነዚህ መሣሪያዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለዓለም ሰላም እና ጸጥታ ስጋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተገቢና ውጤታማ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ የጸጥታ ምክር ቤቱ ያለውን አቋም፤ እነዚህ መሣሪያዎች እንዳይስፋፉ እና እንዳይባዙ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለተደረጉ እና ለሚደረጉ የአገራት ስምምነቶች የጸጥታ ምክር ቤቱ ያለውን ድጋፍ፤ ከእነዚህ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ጋር ተያይዞ የሚደረግ ቁጥጥር አገራት ለሰላማዊ አላማ በቴክኖሎጂ፣ በግብአትና በቁሳቁስ የሚያደርጉትን መደጋገፍና መተባበር የማይጎዳ መሆን እንዳለበት እንዲሁም ለሰላማዊ አላማ በሚደረጉ እንዲህ አይነት ትብብሮች ስም ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ማባዛትና ማስፋፋት እንደማይገባ፤ ከሽብርተኝነት ስጋት ጋር ተያይዞ እነዚህ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች በተለይም በ ተ.መ.ድ. ከተዘረዘሩ የሽብር ድርጅቶች እጅ እንዳይገቡ መከላከልና መቆጣጠር በጣም ወሳኝ መሆኑን፤ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ወይም ግብአቶቹን በሕገወጥ መንገድ ማዘዋወር የዓለም ትልቅ የሰላምና የጸጥታ ስጋት መሆኑን እንዲሁም እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም አገራዊ፣ ክፍለ-አሕጉራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለምዓቀፋዊ የሰመሩ ቅንጅትና ትብብሮችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጥና እነዚህን በማገናዘብ የተሰጠ ውሳኔ ነው፡፡ በዚህም የአገራት ሐላፊነት ምን እንደሆነ አስቀምጧል፡፡
ሁሉም የአለም አገራት ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ወይም ተሸካሚያቸውን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲያበለጽጉ፣ እንዲይዙ፣ እንዲያመርቱ፣ እንዲቀበሉ፣ እንዲያጓጉዙ፣ እንዲያሸጋገሩ ወይም እንዲጠቀሙ የሚያስችል ድጋፍ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ያስቀምጣል፡፡
ሁሉም አገራት የውስጥ ሕጎቻቸው በሚፈቅዱት አግባብ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ወይም ተሸካሚያቸውን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዳያበለጽጉ፣ እንዳይይዙ፣ እንዳያመርቱ፣ እንዳይቀበሉ፣ እንዳያጓጉዙ፣ እንዳያሸጋገሩ ወይም እንዳይጠቀሙ የለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ይህን ተግባር በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል የሚያስችሉ ብቃት ያላቸው ሕጎችን እንዲያወጡ እና እንዲያስፈጽሙ ግዴታ ተጣለባቸው ሲሆንም  ሀገራችንም ይህን ህግ የማውጣት  ግዴታ አለባት ፡፡
በተመድ የጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያን በገንዘብ መደገፍ አስመልክቶ የተወሰነውን ውሳኔ አስመልክቶ (የንዋይ-ቁጥጥር እርምጃ ግብር-ሐይል) (FATF) የተባለ ግብር-ሐይል በምክረ-ሀሳብ 7 ላይ በግልፅ ሀገራት ይህን ድርጊት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ ማውጣት እንዳለባቸው አስቅጧል፡፡
(የንዋይ-ቁጥጥር እርምጃ ግብር-ሐይል) (FATF) በአለማቀፍ ደረጃ የሀገራትን የፋይናንስ ስርአት እያጠና ሪፖርት የሚያወጣ ድርጅት ሲሆን፣ ይህ ድርጅት የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በሀገራት የኢኮኖሚ ስርት በተለይ የፋይናንስ ስርአት ላይ ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ይህ ድርጅት የሀገራትን የፋይናስ ስርአት የሚገመግምበት 40 ምክረ ሀሳቦች ያሉት ሲሆን ከነዚህ ምክረሀሳቦች አንፃር የሀገራትን የፋይናንስ ስርአት እየገመገም የሀገራትን የፋይናንስ ስርአት ተባባሪ ያልሆነ፣ ተባባሪ የሆኑ በጣም ተባባሪ የሆኑ የሚል ደረጃ ይሰጣቸዋል፡፡ የአለም ድርጅቶች ለምሳሌም የአለም ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዚህ ድርጅት ጋር ሚሰሩ ሲሆን የአለም ሀገራትም የዚህን ድርጅት ሪፖርት እነደ አስገዳጅ መስፈርት የሚወስዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም የዚህን ድርጅት ምክረ ሀሳቦች ማሟላት አስገዳጅ ስርአት ሆኗል፡፡
የሀገራችንን ፋይናንስ ስርአት በተመለከተ የአለም ባንክ በ2015 እ.አ.አ. ጥናት ያደረገ ሲሆን ይህን ጥናት (የንዋይ-ቁጥጥር እርምጃ ግብር-ሐይል) (FATF) ሞዴል የሆነው ESAAMLG ሪፖርቱን ወስዶ ያጸደቀወ ሲሆን ይህን ሪፖርት (የንዋይ-ቁጥጥር እርምጃ ግብር-ሐይል) (FATF)ም እንዳለ አፅድቆ የሪፖርቱ አካል አድርጎታል፡፡ በዚህ ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርአት ውስጥ እንደ ትልቅ ክፍተት ከታዩ ጉዳዮች መካከል የጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ብዜት ተግባርን  በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመመቆጣጠር የሚያስችል የህግ  ማእቀፍ አለመኖሩ ነው፡፡
በመሆኑም ይህ ህግ ሀገራችን የላትም ማለት አንደኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በውሳኔ ቁጥር 1540/2004  መሰረት ያስተላለፈውን ውሳኔ አልተወጣችም፣ ሁለተኛ የንዋይ ቁጥጥር እርምጃ ግብር-ሐይል) (FATF) በምክረ ሀሳብ 7 ላይ ያሰፈረውን ሀገራት የጅምላጨራሽ የጦር መሳሪያ ብዜትን ለመከላከል የሚያስችል የህግ ማእቀፍ አላሟላንም ማለት ነው፡፡
በአሁኑ ሰአት ሀገራችን ይህን ህግ ባለማውጣታችን ከዚህ መስፈርት አንፃር እንደነ ኢራቅና የመን ተባባሪ ያልሆኑ ሀገራት ደረጃ ሰጥቷታል፡፡ ይህ ማለት ወደ ሀገራችን የሚተላለፉ ገንዘቦችና የኢንቨስትመንት ስራዎች እንዳይመጡ እንቅፋት የሚሆን ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፉ ገንዘቦች በሙሉ በጥርጣሪ የሚታዩ በመሆኑ በንኮች የማጣራት ስራ ስለመሰሩ የመዘግየት ሁኔታም ይኖራል፡፡ ይህ ደግሞ በበኩሉ ኢንቨስተሮችና ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ አይበረታቱም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ህግ ባለመኖሩ የፀጥታው ምክር ቤት ለጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ብዜት ድጋፍ  የሚዉሉ ናቸው ያላቸውን በተለያ ሀገራት ባንኮችና በግለሰቦች ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ገንዘቦችን በሀገራችን በተገኙ ጊዜ እንድናግድና እንዲወረሱ ትእዛዝ እንዲሰጥ ሲወስን የህግ ማእቀፍ ባለመኖሩ ይህን ውሳኔ እና ትእዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ አንችልም፡፡
ሀገራችን የንዋየ ቁጥጥር እርምጃ ግብር-ሐይል) (FATF) ያስቀመጣቸውን ምክረ ሀሳቦች ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ሲሆን ከዚህ ድርጅት ዝርዝር ውስጥ ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የዚህን ድርጅት ሪፖርቶች አፈፃፀም የሚከታተለው ግብረ ሀይል ለኢትዮጵያ ይህን ህግ የምታወጣበትን ጊዜ ገደብ አስቀምጦ መፀደቁን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ይህ ግብረ ሀይል በክፍተት ያነሳቸውን ጉዳዮች ለመድፈን፣
 
ሀገራችን ከጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ጋር ተያይዞ ከፈረመቻቸው ብዛት ያላቸው ዓለም-ዓቀፍ ስምምነቶች አንጻር ሲታይ ጉዳዩን በልዩ ትኩረት የሚገዛ ሁሉንም ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች በተሟላ፣ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ ያገናዘበ ሕግ ስለሌለን እና በአሁኑ ሰአት የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜት እና ይህንኑ በገንዘብ መደገፍ ዓለም-ዓቀፍ የደህንነት ስጋት ሲሆን፤ ሁሉም አገራት ይህን ለመከላከል፣ ለመግታት እና ለመቆጣጠር በሚደረጉ ሉላዊ የትብብር ማዕቀፎች በጋራ እና በትብብር እንዲሰሩ የሚያስገድድ በመሆኑ እና ሀገራችንም  የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ጋር ተዛማጅነት ያላቸዉ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን ያጸደቀች ሲሆን፤  በስምምነቶቹ የተጣሉባትን  ኃላፊነቶች ለመወጣት አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሀገራችን የጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ብዜትን ለመደገፍ የሚውል ገንዘብ ወይም የዋለ ገንዘብ ቢገኝ ይህን ድርጊት ወንጀል የሚያደርግ እና ገንዘቡን ለመውረስ የሚያስችል የህግ ስርአት ባለመኖሩ  እርምጃ መውሰድና ገንዘቡን መውረስ የሚቻልበት ስርአት የለም፡፡ በመሆኑም እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች አዋጁን ለማውጣት በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የአዋጁ አደረጃጀት

አዋጁ በረጅም ርእስ በመግቢያ፣ በአራት ክፍሎች እና በሀያ አንቀፆች የተደራጀ ነው፡፡  ክፍል አንድ ጠቅላላ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን በስሩም አጭር ርዕስ፣ ትርጓሜን እና የኣጁን የተፈጻሚነት ወሰን በተመለከተ አካቷል፡፡ ክፍል ሁለት ስለ አስፈጻሚ አካላት የሚደነግግ ሲሆን፣ የብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋም፣ ስለ ኮሚቴው አደረጃጀት፣ ስለኮሚቴው ስልጣንና ተግባራት፣ ሰለ ኮሚቴው ስብሰባ ስርአት፣ የሚያወራ ክፍል አለው፡፡
በክፍል ሦሥት ስር የጅምላ ጨራሽ  መሣሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ስለመከላከል፣ መግታትና  መቆጣጠርን የሚመለከቱ ድንጋዎች የተካተቱ ሲሆን ስለ ክልከላዎች፣ ኢላማ የገንዘብና የንብረት ቁጥጥሮችና ማዕቀቦች፣  እርምጃ-ተኮር መረጃ ስለመስጠት እና ስለ ማዕቀቦች፣ ከእግድ ነጻ ሊደረጉ ስለሚችሉ እንዲሁም እገዳ ነጻ ስለሆኑ ገንዘቦች፣ ንብረቶች እና ኃብቶች እንዲሁም  ስለ ኢላማ የገንዘብና የንብረት ቁጥጥሮችና ማዕቀቦችን ማንሳትን የሚመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎችን አካቷ፡፡
ክፍል አራት   ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን ያካተተ ክፍል ሲሆን ስለ ወንጀል ቅጣቶች፣ስለ ሌሎች ሕጎች ተፈጻሚነት ደንብ እና መመሪያ ስለማውጣት ስልጣን እና  አዋጁ ስለ ሚጸናበት ጊዜ አመልክቷል፡፡
የአዋጁ ዝርዝር ይዘት
በክፍል አንድ ጠቅላላ ድንጋጌዎች ስር ከተካተቱት ድንጋጌዎች መካከል አንዱ አንቀፅ አንድ አጭር ርዕስ ነው፡፡ የአዋጁ አጭር ርእስ “የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ” እንዲሆን የተደረገ ሲሆን ይህም የሚከለከለው ተግባር ምን እንደሆነ በጭሩ ስለሚያመለክት በዚህ አግባብ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ ሌላው በአንቀፅ ሁለት ላይ ትርጓሜ የተሰጣቸው ቃላት የተመለከቱ ሲሆን በአዋጁ ውስጥ በተደጋጋሚ በስራ ላይ የዋሉ እና ለተጠቃሚ ግልፅ እንዲሆኑ የሚፈለጉ ወይም እስከአሁን ባለው ሁኔታ ለትርጉም የተጋለጡ   ቃላትና ሀረጋት ትርጉም ተሰጥቷቸዋል፡፡ በመሆኑም “ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች” ፣ “ተሸካሚ” “የጅምላ ጨራሽ መሣሪያ እቅድ” “ብዜት”፣ እንዲሁም  “የፋይናንስ ተቋም” ማለት ምን ማለት እንደሆኑ ከአዋጁ አጠቃቀም አንፃር ትርጉም ተሰጥቷዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ  ለዚህ አዋጅ አተገባበር በጣም አስፈላጊ በመሆናቸው፣ የሪል ስቴት ወኪሎችና ደላሎች፤  የከበሩ ድንጋዮች ወይም የከበሩ ብረቶች ነጋዴዎች፤ የሚከተሉትን ለደንበኞቻቸው የሚያዘጋጁ፣ የሚፈጽሙ ወይም የሚያከናውኑ ጠበቆች፣ ኖታሪዎች እና ራሳቸውን ችለው የሚሠሩ ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች፡- ሪል ስቴት መግዛትና መሸጥ፤ የደንበኛቸውን ገንዘብ፣ ዋስትናዎችን ወይም ሌላ ሐብትን ማስተዳደር፤ የባንክ፣ የቁጠባ ወይም የዋስትና ሂሳቦችን ማስተዳደር፤ ኩባንያ ለመመስረት፣ ለማካሄድ ወይም ለማስተዳደር የሚደረጉ መዋጮዎችን ማስተባበርና ማደራጀት፤ ወይም የሕግ ሰዉነት ያላቸውን ተቋማት መመስረት፣ ሥራቸውን ማስኼድ ወይም ማስተዳደር እንዲሁም የንግድ ተቋማትን መግዛትና መሸጥ፤ ራሳቸዉን ችለዉ የተቋቋሙ የሂሳብ ባለሙያዎች፤  በማዕከሉ የሚሰየሙ ሌሎች የንግድና የሙያ ሥራዎች ምንም እንኳን በቀጥታ የፋይናንስ ተቋማት ባይሆንም “የተሰየሙ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የንግድና የሙያ ሥራዎች” በሚል ትርጉም እንዲሰጣቸው የተደረገ ሲሆን “ማዕከል” ማለት የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል መሆኑም ተመልክቷል፡፡
የአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜት በገንዘብ መደገፍን በተመለከተ መሆኑ በአንቀፅ 3 ላይ የተመለከተ ሲሆን ሆኖም ግን  ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ከማብዛት ውጭ ለሆነ አላማና  ተግባር የሚውሉ የኒኩለር፣ ኬሚካል እና ስነሕይወታዊ ቁሶችን በተመለከተ ተፈጻሚ እንደማይሆን ተመልክቷል፡፡ ሆኖም ግን የድንጋጌው አገላለፅ የበለጸ ግልፅ እንዲሆን ለማድረግ ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ሥምምነቶች የገባቻቸውን ግዴታዎች ከመፈጸም አንጻር የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚከለክል ሆኖ እንደማይተረጎምም ተመልክቷል፡፡
በአንቀፅ 4 ላይ “የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ፀረ-ብዜት ብሔራዊ ኮሚቴ” የተቋቋመ ሲሆን፣ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ እንዲሆን የተደረገበት ዋናው ምክንያት ጉዳዩ ሀገራዊ ይዘት ያለው እና ከሰዎች መሰረታዊ መብቶች ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ በመሆኑ እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተሰጠው ሀላፊነት ብዙ በመሆኑ አና  የሚኒስትሮች ምክር ቤትን በበላይነት የሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ ኮሚቴው ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በአንቀፅ 5 ላይ እንደተመለከተው  የኮሚቴው ሰብሳቢ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒሰትር  ሲሆን በአባልነትም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የጠቅላይ ዐቃቤ-ሕግ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ-ሕግ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ኮሚሽነር፣ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና ሌሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አባል እንዲሆኑ የሚሰየሙ የመንግስት አካላትን የሚያካትት እንዲሆን ተደርጓል፡፡  እነዚህ አካላት አባል እንዲሆኑ የተመረጡት ለጉዳዩ ካላቸው ቅርበት አንፃር ነው፡፡
በአዋጁ አንቀፅ 6 ላይ የኮሚቴው ስልጣንና ተግባር የተመለከተ ሲሆን ይህውም በአገሪቱ የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜት እና ይህን በገንዘብ መደገፍን በተመለከተ ስላለው ሁኔታ በመገምገም ድርጊቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን እና አመራሮችን  የመስጠት፣ መመሪያዎችን የማውጣት፤ ከጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትና ይህን በገንዘብ ከመደገፍ ጋር ተያይዞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሚወሰኑ ቅጣቶችና ማዕቀቦች መፈጸማቸውን የመከታተል፤ በአገር ውስጥም ሆነ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚጣሉ ቅጣቶችና ማዕቀቦች በአግባቡ እና በጊዜ እንዲፈጸሙ ለማድረግ የሚያስችል ክትትል እና ድጋፍ የመስጠት፤ የጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎች ብዜትን በተመለከተ ከፍተኛ ስጋት ናቸው የሚባሉ ግብይቶችን እና ደንበኞችን ዝርዝር ማዘጋጀትና ለፋይናንስ ተቋማትና ለተሰየሙ ፋይናንስ ያልሆኑ ተቋማት መመሪያዎችን ማዘጋጀት፤
እንደአስፈላጊነቱ ይህን አዋጅ በሚገባ ለማስፈጸም የሚረዱ ሀገራዊ ግብረሀይሎችን የማቋቋም ስልጣንና ተግባራት እንዳሉት ተመልክቷል፡፡ ግብረሀይሉን በዚህ ኮሚቴ አማካኝነት እንዲቋቋም የተደረገው ኮሚቴው እንደሁኔታው እያየ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ግብረሀይሎችን ማቋቋም እንዲችል እድሉን ለመስጠት ነው፡፡
በአንቀፅ 8 ላይ ክልከላዎችን አስመልክቶ የተደነገገ ሲሆን በዚሁ አግባብ ማንኛውም ሰው የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን ወይም እቅድን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ በተሟላ ሁኔታም ይሁን በከፊል በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በንብረት፣ በኢኮኖሚያዊ ኃብቶች፣ በገንዘብ ነክ አገልግሎት ወይም በቴክኒካዊና ሙያዊ አስተዋፅዖ መደገፍ የተከለከለ መሆኑ የተደነገገ ሲሆን፣ በአንቀፅ 9 ላይ ደግሞ ኢላማ የገንዘብና የንብረት ቁጥጥሮችና ማዕቀቦችን በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ የተጠቀሰን ግለሰብ ወይም ድርጅት ሂሳብ ወይም ንብረት እና ማናቸውም ዋጋ ያላቸው ሐብቶቹን የሚያግድ፤ ለግለሰቡ ወይም ለድርጅቱ እንዲሁም ለእርሱ ወይም ስለእርሱ በሚሰሩ ወይም በእርሱ ታዘው ለሚሰሩ ሰዎች ተደራሽ እንዳይሆኑ የሚከለክል ውሳኔን እንደሚያሳልፍ፣ ውሳኔውን ሲወስንም የሰጠው እግድ ወይም ክልከላ ስለሚፈጸምበት ዝርዝር ሁኔታ እና ክልከላው ወይም እግዱ የሚቆይበትንም ጊዜ ወስኖ ማስቀመጥ ይኖርበታል፤ ትዕዛዙም ሰፊ ተደራሽነት ባለው ጋዜጣ እንዲታተም እንደሚያደርግ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትዕዛዝ በጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት እለት ጀምሮ የፋይናንስ ተቋማት እና የተሰየሙ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የንግድና የሙያ ሥራዎችን ጨምሮ ማናቸውም ሰዎች በውሳኔው በተጠቀሱ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በሙሉም ሆነ በከፊል፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በባለቤትነት ወይም በይዞታቸው ስር ያሉ፣ ገንዘብ፣ ሌላ ንብረት እና ኃብታቸውን ሁሉ አግደው መያዝ እንዳለባቸው፣ በውሳኔው የተጠቀሱ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በባለቤትነት ወይም በይዞታ፤ በሙሉም ሆነ በከፊል፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከያዙት ገንዘብ፣ ሌላ ንብረት ወይም ኃብቶች የመነጩ ገንዘብ፣ ሌላ ንብረት ወይም ኃብቶችን  ሁሉ አግደው እንዲይዙ አዋጁ ያስገድዳቸዋል፡፡
ተጓዳኝ ግብይቶችን እንዲሁም በዚህ አዋጅ በተደነገገው አግባብ አግደው ስለያዙት ገንዘብ፣ ሌላ ንብረት ወይም ኃብት ወይም ስለወሰዱት ሌላ እርምጃ በ 24 ሰዓት ውስጥ   ለማዕከሉ ማሳወቅ ያለባቸው ሲሆን፣ በማዕከሉ ካልተፈቀደ በስተቀር የታገዱ ገንዘቦችን፣ ሌላ ንብረት ወይም ኃብቶችን መስጠት ወይም መልቀቅ እንደሌለባቸውም ተመልክቷል፡፡እንዲሁም  የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜት በገንዘብ የመርዳት ድርጊት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ድርጅቶችን ለመሰየም ስሙ የተጠቀሰ ሰው ሰው በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል ወይም ለተ.መ.ድ በቀጥታ በማመልከትና እንዲሰየሙ ማስደረግ  የሚቻል መሆኑም ተምልክቷል፡፡  
በአንቀፅ 10 ላይ እርምጃ-ተኮር መረጃ ስለመስጠት እና ማዕቀቦች የተደነገገ ሲሆን፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የተሰየሙ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የንግድ እና የሙያ ተቋማትና ሥራዎች ከፍተኛ የስጋት ተጋላጭነት ያላቸው ደንበኞችን እና ግብይቶችን የመለየት፣ የእነዚህን ደንበኞች እና ግብይቶች እንቅስቃሴ የሚከታተሉበት ልዩ የክትትል ስርአት የመዘርጋት እና ተገቢ የሆነ የክትትል እርምት እርምጃ  የመውሰድ ኃላፊነት እንዳለባቸው፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የተሰየሙ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የንግድ እና የሙያ ተቋማትና ሥራዎች ከፍተኛ የስጋት ተጋላጭነት ያላቸው ደንበኞችን እና ግብይቶችን ሲለዩም፣ በማዕከሉ የሚወጡ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን በገንዘብ ስለመደገፍ አመላካች የሆኑ አግባብነት  ያላቸው መረጃዎችን፤ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ከመከላከልና፣ ከመቆጣጠር ጋር ተያይዘው ካሉ ግዴታዎች አንጻር የተሰበሰቡ ስለደንበኞች እና ስለግብይቶች የተመለከቱ መረጃዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት እና የተሰየሙ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የንግድ እና የሙያ ተቋማትና ሥራዎች ከጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ምክንያታዊ በሆነ መልኩ በሚጠረጠሩ ደንበኞች እና ግብይቶች ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ለማስቻል በጊዜ ለማዕከሉ ማሳወቅ እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡
የሚወሰዱ   እርምጃዎች ለምሳሌ እግዶች ፍትሀዊ እና ህግን የተከተሉ መሆን ስለሚኖርባቸው ማእከሉ እንዲያውቀው ከተደረገው  ግብይት ጋር የተያያዙ ገንዘብ፣ ሌላ ንብረት እና ኃብትን ከአስር ቀናት ላልበለጠ ጊዜ ታግዶ እንዲያዝ ለማዘዝ ይችላል፤ ሆኖም ይህን እርምጃ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ-ሕግ ወዲያውኑ ማስታወቅ እንዳለበትና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ-ሕግም አግባብነቱን በመመርመር የተሰጠ የእግድ ትዕዛዝ እንዲጸና እና እንዲራዘም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማመልከት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡
አንዳንድ ገንዘቦች፣ ንብረቶችና ሀብቶች እግድ ሊደረግባቸው የማገባበት ሁኔታ አለ፡፡ በመሆኑም በአንቀፅ 11 ላይ ከእግድ ነጻ ሊደረጉ ስለሚችሉ  ገንዘቦች፣ ንብረቶች እና ኃብቶች የተዘረዘረ ሲሆን፣  በኪራይ ወይም በዋስትና ክፍያዎች፣ በደመወዝ፣ በግብርና በቀረጥ፣ በመድህን አረቦን፣ በሕዝባዊ አገልግሎት ክፍያዎች ወይም በሕግ ሙያ አገልግሎት ክፍያዎች ላይ፤ ሦሥተኛ ወገኖች በቅን ልቦና በያዟቸው ገንዘቦች፣ ንብረቶች ወይም ሌሎች ኃብቶች ላይ፤ በንብረት አስተዳዳሪ እና በሂሳብ አጣሪ የሙያ ክፍያዎች  ከእግድ ነጻ ሊደረጉ የሚችሉ ሲሆኑ ከውርስ ነጻ መሆናቸው ግን የተጠበቀ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ እነዚህ ንብረቶች ነፃ እንዲሆኑ የተደረገበት ዋናው ምክንያት የህዝብ ሀብት ስለሆኑ እና የሶስተኛ ወገን ባለቅን ልቦናዎችን ጥቅም ላለመጉዳት በማሰብ ነው፡፡
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተጣለ ማእቀብ ወይም እግድ የሚነሳበትን ስርአት መዘርጋት አስፈለጊ በመሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 12 ላይ ይህንኑ ለማመልከት የተሞከረ ሲሆን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን ሲያደርግ ከዚህ አዋጅ ወይም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር አግባብነት ካላቸው ሌሎች ህጎች እንዲሁም ከጉዳዩ አንጻር ኢትዮጵያ በዓለም ኣቀፍ ሥምምነቶች የገባቻቸውን ግዴታዎች በማይጻረር መልኩ መሆን እንዳለበትም ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት  የወሰነውን ውሳኔ ሊያሻሽል ወይም ሊሽር ይችላል ማለት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ይህን ሲያደርግ ውሳኔው እገዳው ወይም ክለከላው ስለሚነሳበት ሁኔታ ዝርዝር የያዘ መሆን የሚገባው ሲሆን፤ ሰፊ ተደራሽነት ባለው ጋዜጣም ታትሞ እንዲወጣ እንደሚያደርግም ተመልክቷል፡፡
ሌላው በአንቀፅ 13 ላይ የተመለከተው ቅጣቾችን አስመልክቶ ነው፡፡                               በዚሁ መሰረት የአዋጁን አንቀጽ 8 እና 9(5)የተላለፈ ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና እስከ አንድ መቶ ሺ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ የተደነገገ ሲሆን፣ ወንጀሉ የተፈጸመው በሕግ ሰውነት በየተሰጠውን አካል በሆነ ጊዜ ከአምስት መቶ ሺ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይቀጣል፡፡
የሌሎች ሕጎች ተፈጻሚነትን በተመለከተ ማእከሉ ስራውን በአግባቡ መስራት እንዲችል ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያዞ አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕጎች የተሰጡት ስልጣንና ተግባራት ለዚህም አዋጅ ተፈጻሚ እንዲሆኑ አዋጁ እውቅና የሰጠ ሲሆን፣ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005፣ አዋጅ ቁጥር 652/2001፣ አዋጅ ቁጥር 881/2007 ያሉ ድንጋጌዎች እንደአግባብነታቸው ለዚህም አዋጅ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ እና በሌሎች ሕጎች ስለ ምርመራ፣ ገንዘብ ወይም ንብረት ስለመያዝ፣ ንብረት ስለማስተዳደር፣ ስለመውረስ፣ ስለተያያዥ  ወንጀሎች እና ስለ ዓለም-ዓቀፍ ትብብር የተመለከቱ አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች ለዚህም አዋጅ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይህ የተደረገበት ምክንያት አዋጁ ሌሎች ህጎችን የሻረ እንዳያስመስልእና ሁሉንም ነገር በዚህ አዋጅ ዘርዝሮ መጨረስ ስለማይቻል ሌሎች ህጎችንም እንደአግባብነቱ መጠቀም እንዲቻል በማሰብ ነው፡፡

ማጠቃለያ

የአገራችን ሕጎች ከጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች አንጻር ያስቀመጧቸው ድንጋጌዎች ጉዳዩን በተገቢ እውቅና፣ ትኩረት እና ቀጥተኛነት አገናዝበው የወጡ ናቸው ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን በተመለከተ ግልጽ፣ ቀጥተኛና ዝርዝር የወንጀል ተግባራትን በሕግ ወስኖ ማስቀመጥ ጉዳዩን በአግባቡ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚኖረው አግባብነት እና ጠቀሜታ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ የአገራችን ሕጎች ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ጋር ተያይዞ ማን ምን ተግባርና ሐላፊነት እንዳለበት በግልጽ ወስነው ያስቀመጡ አይደሉም፡፡ ተገቢ የሆነ የተደራጀ የቁጥጥርና ክትትል ስርአትንም ያስቀመጡ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ይህን ድርጊት በአግባቡ የሚገዛ አዋጅ ማውጣት በማስፈለጉ ይህ ኣዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡

0 (0 Votes)

Quick Reply