Participate Participate

በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት አዋጅ

Threads [ Previous | Next ]

መነሻ ሃሳብ

 1. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላለፉት ተከታታይ 14 ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ 10.6 በመቶ የሆነ ፈጣን ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ይህም፣ ዓመታዊ የዜጐች አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ 863 የአሜሪካን ዶላር ከፍ እንዲል፤ በ1998 ዓ.ም. ከድህነት ወለል በታች ይገኝ የነበረው 45.5 በመቶ የአገሪቱ ሕዝብ በ2008 ዓ.ም. ወደ 23.5 በመቶ ዝቅ እንዲልና የአንድ ሰው በህይወት የመኖር ዕድልም በ2ዐዐዐ ዓ.ም ከነበረበት 54 ዓመት በ2ዐ08 ወደ 64 ዓመት ከፍ እንዲል አስችሎታል፡፡

 2. ይህንን  ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠልና የፋይናንሱ ዘርፍ ለኢኮኖሚው ዕድገትና መረጋጋት እስከ አሁን ያበረከተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የበለጠ ለማሳደግ ሥርዓቱን በሂደት ዘመናዊና አካታች እንዲሆን ማድረግ አማራጭ የለውም፡፡ ቁጠባን በማሰባሰብ በቂና ቀጣይነት ያለው የብድር አገልግሎት በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላለው ህብረተሰብ፣ ለግብርናው ዘርፍ፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በማቅረብ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና በሂደቱም የሥራ ዕድልን ለማስፋፋት፣  ምርትና ምርታማነትን ለመሳደግና ድህነትን ለመቀነስ የተጀመረውን ትግልና አቅጣጫ በሰፊው ለመደገፍ ያስችላል፡፡

 3. የአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ ቢሆንም አሁንም ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጐች ከድህነት ወለል በታች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ዜጐች ከድህነት ለማውጣት የፋይናንስ ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን ማስፋፋትና ማሳደግ ወሳኝ ሚና የሚጫወት  ቢሆንም የፋይናንስ ዘርፉ አገልግሎት በዋናነት በከተሞች ላይ ብቻ ተወስኖ በመቆየቱ የግብርናው ዘርፍ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ በቂ የፋይናንስ አገልግሎት በማግኘት ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ሰፊ መሠረት ካለው ህብረተሰብ ሊገኝ የሚችልን እምቅ ሀብት ወደ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት በማስገባት ወደ ውጤት መቀየር አልተቻለም፡፡

 4. ለዚህም አንዱና መሠረታዊው ውስንነት የብድር ሥርዓቱ በዋናነት በማይንቀሳቀስ ንብረት መያዥ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ተንቀሳቃሽ ንብረትን ለብድር መያዣነት በመጠቀም ሥራ ላይ የሚውል አዲስ ካፒታል ለማመንጨት የሚያስችል  የሕግ ማዕቀፍና የአሠራር ሥርዓት አለመኖር ነው፡፡

 5. በአሁኑ ወቅት ለብድር ዋስትና በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት የመኖሪያና የአገልግሎት ሕንፃዎች፣ የንግድ ተቋማት፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ናቸው፡፡ ይህ ዓይነት ንብረት ሊኖረው የሚችለው የህብረተሰብ ክፍል በአንፃራዊነት በጣም ትንሽ በመሆኑ፤ ብዙው ህብረተሰብም ሆነ አነስትኛ ተቋማት ያላቸውን ተንቀሳቃሽ ንብረት ለብድር መያዥነት እንዲውል በማስቻልና በፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ በማስገባት አዲስ ሥራ ላይ የሚውል ካፒታል መፍጠር ባለመቻሉ ለብድር አገልግሎትና ተደራሽነት ውስንነት  መሠረታዊ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

 6. በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የፋይናንስ ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ካላቸው ሀገሮች መካከል ትገኛለች፡፡ ይህም ያሳደረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመገንዘብና ችግሩንም ለመቅርፍ ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ተቀርጾ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ ሲሆን ሙሉ ትግበራውም በ2ዐ1ዐ ዓ.ም መጀመሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይፋ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሠረትም ሥራዎች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን የስትራቴጂው አንዱ አካል የሆነው በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ ዋስትና መብት አዋጅ ተረቋል፡፡

 7. አዋጁ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የተመሠረተ ዕምቅ የብድር ፍላጎት ህጋዊ መሠረት በማስያዝና አስተማማኝ ሥርዓት በመዘርጋት ለአገልግሎቱ አቅራቢም ሆነ ተጠቃሚ ምቹ ሁኔታን በዘላቂነት ለመፍጠር ያስችላል፡፡ በሂደትም ኢንቨስትመንትን በየደረጃው ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ምርትና ምርታማነትን በተለይም በግብርናው ዘርፍ፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች እና ዝቅተኛ ገቢ ባለው ህብረተሰብ ዙሪያ ለማሳደግ አስተማማኝ መሠረት ይጥላል፡፡ ሀገራችን ከድህነት ለመውጣት በምታደረገው ትግልና የዕድገት አቅጣጫ ላይም ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡

 8. አዋጁ በUnited Nation Commission on International Trade law( UNCITRAL) ሕግ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ አለም አቀፋዊ ይዘት አለው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ በDoing Business የምዘና መሥፈርት ያላትን ዝቅተኛ ደረጃ (በ2017 ከ190 የዓለም ሀገራት 159ኛ ነበረች) ከፍ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከሚጠየቁ መሥፈርቶች አንዱ በመሆኑ በዚሁ ዙሪያ ይታይ የነበረውን ክፍተት ለመዝጋት ያስችላል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሥልጣን ምንጭ

 1. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማቋቋሚያ (እንደተሻሻለው) አዋጅ ቁጥር 591/2ዐዐዐ አንቀጽ 4 መሠረት ባንኩ ከተቋቋመበት ዓላማዎች መካከል ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት መገንባት እና ለኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት አመቺ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን አንዱ ነው፡፡  እንዲሁም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 5 ስር ለባንኩ ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባር አንዱ የባንክ እና የሌሎች የገንዘብ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው፡፡

 2. የአገራችንን የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ቁጠባን በማሰባሰብ የብድር አገልግሎትን ለማቅረብ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና በሂደቱም የሥራ ዕድልን ለማስፋፋት፣  ምርትና ምርታማነትን ለመሳደግና ድህነትን መቀነስ ዓላማው ያደረገ ብሔራዊ ስትራቴጂ እንዲቀረፅ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መሪነት የብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ካውንስል ተቋቁሞ አቅጣጫ በተሰጠው መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ተረቆና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ስራ በተገባው ሰነድ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብድር አሰጣጥ ስርአቱን ለማዘመን እንዲያስችል ይህን በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት ረቂቅ አዋጅን አዘጋጅቷል፡፡    

 • አዋጁ ዓላማዎች

 1. የአዋጅ መሠረታዊ አላማዎች፡-

  • / ተነቀሳቃሽ ንብረትን ለብድር ዋስትና በማስያዝ በተለይም የግብርናው ዘርፍ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ እና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለኢንቨስትመንት የሚሆን ካፒታል ማግኘት የሚችሉበትን ሕጋዊ መሠረት መጣል፣
 • /    ሥርዓቱን በመዘርጋትና ለብድር ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በየደረጃው ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣

 • /   ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን መፍጠርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣

 • /  በዋናነት በከተሞች ላይ ብቻ ውስን ሆኖ የቆየውን የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎትና ተደራሽነት ወደ ገጠሩ ማህበረሰብ ለማስፋፋትና ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን መፍጠር፤

 • / ሕጋዊ፣ ዘመናዊ፣ ቀጣይና ተዓማኒነቱ የተረጋገጠ የብድር ዋስትና ሥርዓት በመዘርጋት፣ የማስፈፀሚያ መንገዱንም ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን በማስቻል ለብድር አገልግሎት አቅራቢውም ሆነ ተጠቃሚው አስተማማኝና በህግ ማዕቀፍ የተደገፈ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ፤ እና

 • /    በፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ውስጥ የተቀመጡ ግቦችን ማሳካት፤ 

 1. ለዚህም፣ ለብድር ዋስትና የሚያዝ ተንቀሳቃሽ ንብረትን ወጥና ለተጠቃሚው ክፍት የሆነ ማዕከላዊ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓትን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያከናውን ተቋም በመመሥረት፣ በዋስትና የተያዘ ንብረት ላይ የቀዳሚነት መብትን ለመወሰን የሚያስችል በሕግ ማዕቀፍ ላይ የተመሰረተ ሥርዓት ይዘረጋል፡፡

የረቂቅ አዋጁ የዝግጅት ሒደት

 1. አዋጁን በማርቀቅ ሂደት የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ድጋፍ የተገኘ ሲሆን ይዘቱም UNCITRAL ሕግ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህንን ሕግ በመተግበር ቀዳሚ ልምድ ያላቸው ሁለት የአፍሪካ አገሮች (ማላዊና ዛምቢያ) ተሞክሮዎችን በማጥናት ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም ተሞክሯል፡፡ በማርቀቅ ሂደቱ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ከሌሎች የፋይናንስ ዘርፉ የተወጣጡ የህግ ባለሙያዎችን ያካተተ የሥራ ቡድን (working Group)  በማቋቋም የአዋጁ ይዘት አሁን በሥራ ላይ ካሉ ሕጎች ጋር እንዲጣጣም ተደርጓል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ፣ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ ከባንኮች ማህበርና ከህግ ባለሙያዎች ማህበር ግብዓት በጽሁፍ በማሰባሰብና በማካተት አዋጁ እንዲዳብር ተደርጓል፡፡ በመነሻ ጥናቱ ላይና በመጨረሻ ረቂቁ ላይ ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ሁለት የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ሰፊ ግብዓት ተሰብስቧል፡፡ ከዚህም የተገኙና ጠቃሚ የሆኑ ምክረ ሀሳቦችን በማካተት  አዋጁ አሁን ያለውን ቅርጽና ይዘት እንዲኖረው ተደረጎ ተረቋል፡፡

የረቂቅ አዋጁ ይዘት

 1. ይህ አዋጅ በስምንት ክፍሎች የታቀፋ 96 አንቀፆች ያሉት ሲሆን በሥራ ላይ ከሚገኘው የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት አሠራርና የንግድ ሥርዓቱ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በክፍል አንድ ሰፋ ያሉ ትርጓሜዎች ተካተዋል፡፡ የአዋጁ የተፈፃሚነት ወሰንም እንዲመሠረት ተደርጓል፡፡

 2. በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የዋስትና መብት አመሠራረት ሒደት በክፍል ሁለት ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት ከአንቀጽ 4-12 በስምምነት ስለሚመሠረት የዋስትና መብት እና ይዘቱ፣ ዋስትናቸው ሊጠበቅ የሚችሉ ግዴታዎች፣ በዋስትና ስለሚያዘው ንብረትና የዋስትና ግዴታ መግለጫ ይዘትን፣ በዋስትና የተያዘ ተንቀሳቃሽ ንብረት በሚያፈራው ሀብት ላይ ስለሚኖር መብት፣ በዋስትና የተያዘ ንብረት ከሌላ ውህድ ወይም ምርት ጋር የተቀላቀለ እንደሆነ የመብት ጥያቄው ስለሚመለስበት፣ በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የብድር ዋስትና እንዳይመሰርት የሚገድቡ ምክንያቶች፣ ግዑዝነት በሌለው ሀብት ወይም በተላላፊ የገንዘብ ሰነዶች ላይ ዋስትና ያገኘ አበዳሪ ዋስትናውን ለክፍያ ወይም ለሌላ ግዴታ ማስፈጸሚያ እንዴት መጠቀም እንደሚችል፣ መያዣውን ለሌላ ማስተላለፍ ቢፈልግ መከተል የሚኖርበት የሕግ ሒደት እንዲሁም በተላላፊ ሠነድ የተሸፈነ ግዑዝ ሀብት ላይ ስለሚኖር መብት በዝርዝር ተደንግጓል፡፡

 3. የቀዳሚነት መብት በአመዘጋገብ ቅደም ተከተል መሠረት እንደሚሆንና የዋስትና መብት በሦስተኛ ወገን ላይ ስለሚኖረው ተፈጻሚነትና ተፈፃሚ የሚሆንበት መንገድ በክፍል ሶስት ሥር  ከአንቀጽ 13-19  በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

 4. ስለመያዣ ምዝገባ ጽ/ቤት መቋቋም፣ እንዲሁም መያዣ ሰጪው መያዣውን ለማስመዝገብ ማሟላት ስለሚጠበቅበት መስፈርቶች፣ የመያዣ ምዝገባ ጽ/ቤቱ የተመዘገቡ መያዣዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግና በሕግ አግባብ መረጃ መስጠት እንደሚጠበቅበት፣ በተመዘገበ መያዣ ላይ ማሻሻያ ወይም ስረዛ ስለሚደረግበት  ሁኔታ፣ ከምዝገባ በኋላ መያዣውን ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ስለሚፈቀድበት አግባብ፣ የመያዣ መዝገብ ውስጥ የሰፈረ መረጃ ስለሚደረግለት ጥበቃ፣ መረጃን ከመያዣ መዝገብ እና ማህደር ማስወገድ ስለሚቻልበት የሕግ አግባብ  እንዲሁም የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የተጠያቂነት ወሰንን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በክፍል 4 ከአንቀጽ 20 እስከ 44 ባሉት አንቀጾች በዝርዝር ተደንግገዋል፡፡

 5. በክፍል አምስት፡- 

  • ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በመያዣው ላይ ስለሚኖረው የቀዳሚነት መብት፣ በአንድ  ወይም በተለያዩ መያዣ ሰጪዎች ተደራራቢ መብቶች ቢፈጠሩ ወይም በተለያዩ ዋስትና ሰጪዎች ተወዳዳሪ መብቶች ቢፈጠሩ የቀዳሚነት መብት እንዴት ሊወሰን እንደሚችል፤
 • ዋስትና የተመሠረተበት መንገድ በሚለወጥበት ጊዜ የተወዳዳሪ መብቶች ቀዳሚነት እንዴት እንደሚወሰን፣ በተያያዥ ገቢ ላይ ስለሚኖር የቀዳሚነት መብት፣ ውህድ ወይም የተቀላቀሉ ግዑዝ ሀብቶች ላይና በቋሚ ንብረት ተጓዳኞች ላይ የተሰጠ ዋስትና የቀዳሚነት መብት እንዴት እንደሚወሰን፤

 • መያዣውን የገዛ፣ የተላለፈለት፣ የተከራየ፣ ወይም እንዲጠቀም ፈቃድ የተሰጠው ሰው መብቶች እና በሕግ የገንዘብ ጠያቂነት መብት የተሰጠው ሰው መብቶች፤

 • ከተገኘ የዋስትና መብት ጋር የሚወዳደር ሌላ የዋስትና መብት ቀዳሚነት እንዲሁም የተገኘ የዋስትና መብት ላይ የሚነሳ ተወዳዳሪ መብት ቀዳሚነት የሚወሰኑባቸው አግባቦች፤

 • በአዕምሯዊ ንብረት ወይም በንግድ ዕቃ ላይ የተገኘ ቀዳሚ የዋስትና መብት የንብረቱ ተያያዥ ገቢ ላይም የቀዳሚነት መብት እንደሚኖረው፤ ከውህድ ወይም ምርት ጋር የተቀላቀሉ ግዑዝ ሀብቶች ላይ የተገኘ መብት ቀዳሚነትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችና  የቀዳሚነት መብትን ስለመተው፣  እና

 • በዋስትና የተያዙ የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶች፣ ወደ ባንክ ሒሳብ የሚገባ ተከፋይ ገንዘብ ላይ የቀዳሚነት መብቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች፣ ለመያዣነት ከዋለ የባንክ ሂሳብ ላይ ዝውውር የተፈጸመለት ሰው ገንዘቡን ከዋስትና ነፃ በሆነ መንገድ ሊያገኝ ስለሚችልበት ሕጋዊ መስፈርት፣  የሚተላለፍ ሰነድን በይዞታው ስር ያደረገ ባለመብት ሰነዱ በሚሸፍነው ንብረት ላይ ተወዳዳሪ መብቶች ቢነሱ የቀዳሚነት መብት እንዴት እንደሚመለስና በሰነድ የተደገፉ ሴኩሪቲዎችን መሠረት በማድረግ ስለሚገኙ የዋስትና መብቶች፣

ከአንቀፅ 45 እስከ 65 ተደንግገዋል፡፡

 1. ክፍል ስድስት እና ሰባት በዋናነት በተዋዋይ ወገኖች እና በሶስተኛ ወገን ላይ ስለሚጣሉ መብትና ግዴታዎች፣  ግዴታ አለመፈፀምን ተከትሎ የገንዘብ ጠያቂው መብቶች፣ የዋስትና ግዴታዎችን በመፈፀም መያዣውን መልሶ የመውሰድ መብቶችን፣ በመያዣ ላይ የሚነሱ ተወዳዳሪ የቀዳሚነት መብቶች እንዴት እንደሚወሰኑና ሌሎች ተያያዥ የዋስትና መብት ማስከበርን የተመለከቱ ድንጋጌዎች  ተሸፍነዋል፡፡

 2. ክፍል ስምንት  ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን ያካተተ ሲሆን በዋናነት የተሻሩ ሕጐች፣ ይህ ረቂቅ ከመጽደቁ አስቀድሞ የጸኑ የዋስትና መብቶች እንዴት እንደሚስተናገዱና ሌሎች የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡

 • በመያዣ ስለተያዘ ንብረት በወጣ አዋጅ ቁጥር ፺፯/፲፱፻፺ ውስጥ በተንቀሳቃሽ ንብረት የመያዣ መብት ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ ድንጋጌዎች በሙሉ በዚህ አዋጅ መሻራቸው በአንቀጽ 89 ላይ ተመልክቷል፡፡         እንደዚሁም ስለንግድ ተቋም የዋስትና መያዣ የወጣ አዋጅ ቁጥር ፺፰/፲፱፻፺ በዚህ አዋጅ ተሽሯል፡፡የተሻሩትም አንቀፆች እንደአግባብነታቸው በዚሁ አዋጅ ውስጥ ተጠቃለው እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

በአንቀጽ 92 ላይ በሌሎች ሕጐችና ድንጋጌዎች መሠረት የትራንስፖርት ሚኒስቴር በተሽከርካሪዎች ላይ፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጋር በተገናኘ፣ የንግድ ሚኒስቴር ከንግድ ተቋማትና ከዱቤ ግዢ ጋር በተገናኘ እና ሌላ ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ከዋስትና ምዝገባ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ያሏቸው መብቶችና ግዴታዎች በዚህ አዋጅ መሠረት ለሚቋቋመው የመያዣ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተላልፈዋል፡፡ ይህም ሆኖ፣ በዋስትና የተያዘ ንብረትን በግዢ ወይም በሽያጭ ሂደት የባለቤትነትን መብት ከማስተላለፋቸው በፊት መብቱ ከዋስትነ ነጻ መሆኑን ከዋስትና መዝገቡ ማጣራትና ማረጋገጥ እንዳለባቸው ሀላፊነት ሰጥቷል፡፡ ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም የሚረዳ ደንብ የማውጣት ሥልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ መመሪያ የማውጣት ሥልጣን ደግሞ ለሚቋቋመው የመያዣ ምዝገባ ጽ/ቤት መሰጠቱ በረቂቁ አንቀጽ 94 ላይ ተደንግገዋል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚቋቋመው የመያዣ ምዝገባ ጽ/ቤት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ እስኪቋቋም ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጽሕፈት ቤቱን በማቋቋም በዚህ አዋጅ የተሰጡ ኃላፊነቶችን እንደሚወጣ በአንቀጽ 95 ላይ የሽግግር ስልጣን ተሰጥቷል፡፡ ማጠቃለያ

 1. ይህ አዋጅ በጥቅሉ ሲታይ ግለሰቦችና ተቋማት ቀጣይና አስተማማኝ የሆነ ብድር አቅርቦት ማግኝት እንዲችሉ፣ ኢንቨስትመንት በየደረጃው እንዲስፋፋ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ ቁጠባ እንዲበረታታ፣ እስከ አሁን የተገኙ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ድሎችን ለማስቀጠልና አገራችን በተያያዘችው የድህነት ቅነሳ ትግልና የዕድገት ጉዞ ላይ የራሱን ጉልህ ድርሻ ያበረክታል፡፡ በመሆኑም አዋጁ በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚመሠረት የብድር ሥርዓትን ቀልጣፋና ዘመናዊ እንዲሁም ለአግልግሎት ሰጪውም ሆነ ተቀባዩ አስተማማኝ መሠረት እንዲጥል ሆኖ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

0 (0 Votes)

Quick Reply